አቶ ዘርአይ አስገዶም ባለቤት ኮለኔል ትርፉ አስፋው በጋምቤላ ባለሶስት ኮከብ ሆቴል ባለቤት መሆናቸውን ምንጮቻችን ገለጹ።

ESAT
(ኢሳት ደሲ–የካቲት 6/2010) የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርና የሕወሃቱ ነባር ታጋይ አቶ ዘርአይ አስገዶም ባለቤት ኮለኔል ትርፉ አስፋው በጋምቤላ ባለሶስት ኮከብ ሆቴል ባለቤት መሆናቸውን ምንጮቻችን ገለጹ። ኮለኔሏ የመከላከያ ጨረታዎችን በመውሰድ ከፍተኛ ሃብት ያካበቱ መሆናቸውም ይነገራል። የአቶ ዘርአይ አስገዶም ልጆችም በአሜሪካ ውድ ትምህርት ቤቶች በመማር ላይ መሆናቸውም ታውቋል።

የአሁኑ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሮድካቲንግ ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ ዘርአይ አስገዶም ከተራ የሕወሃት ተዋጊነት ወደ ሚዲያ ባለስልጣንነት የተሸጋገሩ የአቶ መለስ ዜናዊ የቅርብ ሰው ነበሩ። ምንም ሙያ ሳይኖራቸው የመንግስትን ቴሌቪዥንና ሬዲዮ እንዲመሩ የተደረገውም በወይዘሮ አዜብ ድጋፍ፣በአቶ መለስ ዜናዊ በኩል መሆኑ ይነገራል። አቶ ዘርአይ አስገዶም ቴሌቪዥንና ሬዲዮን ሲመሩ በትራንስሚተር ማስፋፊያና ትልልቅ ጨረታዎች ከፍተኛ የሙስና ቅሌት ውስጥ እንደነበሩም በቅርብ የሚያውቋቸው የመሰክራሉ። በዚሁ የትራንስፎርመር ጨረታ የሚጠረጠሩት የአቶ አስገዶም ባለቤት ኮሎኔል ትርፉ አስፋው ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የተዋጣላቸው ኢንቨስተር መሆናቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። 3 ልጆቻቸውም በአትላንታ ውድ ትምህርት ቤቶች በመማር ላይ ናቸው ተብሏል። እነዚሁ ልጆችም በአትላንታ በተገዛላቸው ቤት ይኖራሉ ነው የተባለው። ኮለኔሏ ከመከላከያ ሚኒስቴር ጡረታ እንዲወጡ ተደርጎ ወደ ኢንቨስትመንት ከገቡ በኋላ በጋምቤላ ባለ 3 ኮከብ ሆቴል መገንባታቸውም ይታወቃል። የመከላከያ ጨረታን በመውሰድም በሃብት ላይ ሃብት እንደሚጨምሩም ነው የሚነገረው።

በጋምቤላ ብረቷ እመቤት የሚል ስም ያላቸው ኮለኔል ትርፉ አስፋው ከበረሃ ታጋይነት ወደ ኮለኔልነት ቀጥሎም ወደ ኢንቨስተርነት ሲሸጋገሩ አቶ ዘርአይ አቶ መለስን መከታ አድርገው ድጋው ይሰጡ እንደነበርም ነው የሚገለጸው። አቶ ዘርአይ በቅርቡ በተካሄደው የብሮድካስት ሚዲያዎች ግምገማ ላይ የትግራይን ቴሌቪዥን ውሸታም ማለታቸውን ተከትሎ በአባባላቸው የተናደዱ ሕወሃቶች ጥርስ እንደነከሱባቸው ይነገራል። በደህንነት ሹሙ አቶ ጌታቸው አሰፋ የሚተማመኑት አቶ ዘርአይ አስገዶም የመንግስት ቃል አቀባዩ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ የሚሰጡትን መግለጫ በማጣጣል የግል አቋማቸው ሊሆን ይችላል በማለት በዝለፋቸውም አይዘነጋም።

https://amharic.ethsat.com/%e1%8b%a8%e1%8b%98%e1%88%ad%e1%…/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *