የእስረኞች መፍታት ብቻውን ለህዝቡ ጥያቄ መልስ አይሆንም!!!

የእስረኞች መፍታት ብቻውን ለህዝቡ ጥያቄ መልስ አይሆንም

ፋሲል የኔአለም

 

በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ መግለጫ ዙሪያ አንድ ነገር ለማለት ሳሰላስል በድንገት የፖለቲከኛ እስረኞች እንደሚፈቱ ተነገረን። የእስረኞች መፈታት ሁላችንንም የሚያስደስት ዜና ቢሆንም፣ ድሮም እነሱ ሳይታሰሩ አፈና እንደነበርና የእነሱ መፈታትም አፈናውን እንደማያቆመው ልብ ማለት ይገባል። የእስረኞች መፍታት ብቻውን ለህዝቡ ጥያቄ መልስ አይሆንም። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተፈተው በነጻ የሚጽፉበት፣ በነጻ የሚደራጁበትና በነጻ ምርጫ ተወዳድረው አላማቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉት ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ይህ አይነቱ ስርዓት የሚዘረጋው ደግሞ ከሁለም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በገለልተኛ አካላት ድርድር ተደርጎ፣ አለም የሚመሰክረው ነጻ ምርጫ ሲደረግና ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር ሲኖር ነው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ስልጣንን በጥገናዊ ለውጥ ለማቆየት ከሚደረግ ሙከራ የተለዬ አይሆንም።

አምባገነን ስርዓቶች ስልጣናቸውን ቢያንስ ከ5ቱ በአንደኛው መንገድ እንደሚያጡ ታሪክ ያስተምረናል።

አንደኛው- መፍንቅለ መንግስት ነው። በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ በርካታ አምባገነን መንግስታት ስልጣናቸው በዚህ መንገድ አጥተዋል። የአፍሪካ ህብረት መፈንቅለ መንግስትን ቢያወግዝም፣ አሁንም በዝምባብዌና ግብጽ ስሙን ቀይሮ እውን ሆኗል።

ሁለተኛው – ህዝባዊ አመጽ ነው። በቱኒዚያ፣ ዩክሬን፣ ሮሜንያ፣ ቼክ ወዘተ በህዝባዊ አመጽ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተደርጓል።

ሶስተኛው- ስልጣን የያዘው አካል ከተቃዋሚዎች ጋር ስልጣኑን በመካፈል አብሮ ገዢ ሆኖ መውጣት ነው። በፖላንድ የጄ/ል ጃሩዘልስኪ መንግስት ከሶሊዳሪቲ እንቅስቃሴ ጋር ያደረገው የስልጣን መካፈል ድርድር ይጠቀሳል።

አራተኛው- መሪዎች በእድሜ ሲገፉ እነሱ ለመረጡዋቸው ሰዎች አስረክበው የሚሄዱበት መንገድ ነው። ኬንያ በዳንኤል አራፕ ሞይ፣ አንጎላ በዶሳንቶስ ፣ ኩባ በፌደል ካስትሮ ዘመን የተካሄደውን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል።

አምስተኛው- አምባገነኖች በአገዛዛቸው ላይ መጠነኛ ለውጥ አድርገው፣ ህዝቡን በለውጥ ተስፋ እያዘናጉ ምክንያታቸው ሁሉ ተሟጦ እስኪያልቅ ድረስ የስልጣን ጊዜያቸውን እያራዘሙ ይቀጥላሉ። ለዚህ ሩስያ ጥሩ ምሳሌ ናት። ጎርባቼቭ በኮሚኒስት ፓርቲ ውስጥ ያደገ apparatchik ነበር። ጎርባቼቭ ነባር ኮሚኒስቶች ማርጀታቸውንና ኮሚኒዝም እስካሁን በመጣበት መንገድ እንደማይቀጥል ሲያወቀው ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን ትንሽ ከፈት በማድረግ በዚሁ ድርጅት ውስጥ የነበሩ ፖለቲከኞች ስልጣን ይዘው እንዲቆዩ የሚያደርግ አሰራር ተከተለ ። ዛሬ ሩስያን የሚገዛት ፑቲን የጎርባቼቭ የእጅ ስራ ውጤት ነው። እነዚህ ሰዎች መጠነኛ የፖለቲካ ለውጥ በማድረግ የሚያጡት ነገር ቢኖር ግለሰባዊ ክብር ነው። ፈላጭ ቆራጭ በነበሩበት ሰዓት ደፍሮ የሚናገራቸው ስለማይኖር ክብራቸው ምንጊዜም እንደተጠበቀ ነው ። የፖለቲካ ሜዳውን ትንሽ ሰፋ ሲያደርጉት በሚደርስባቸው ትችት ክብራቸው የሚነካ ቢሆንም፣ እየተዘለፉም ቢሆንም በስልጣን ላይ ይቆያሉ። ለእነሱ ስልጣን ከግለሰብ ክብር በላይ ነው።

አሁን ህወሃት/ኢህአዴግ ሊከተለው ያሰበው መንገድ እነ ፑቲን የሚሄዱበትን መንገድ ነው፤ ትንሽ ተስፋ በምታጭር ለውጥ ህዝቡን የተስፋ ዳቦ እየመገበ መግዛት ይፈልጋል። ላለፉት 26 ዓመታት ሲጋገር የነበረው የተስፋ ዳቦ የኢኮኖሚ እድገት የሚል ነበር። ዳቦው ሊበላ ባለመቻሉ ህዝቡ ሆ ብሎ ተነሳ። አሁን ደግሞ “የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት” የሚል አዲስ የተሳፋ ዳቦ ይዘው ብቅ አሉ። ይህን የተለመደውን የማታለያ ዘዴ ህዝቡ አምኖ የሚቀበለው አይመስለኝም።

በዚህ ወሳኝ ወቅት ያለው ብቸኛ አማራጭ እስከመጨረሻ መታገልና እውነተኛ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ነው። የተጀመረውን ትግል እስከመጨረሻው በብልጠትና በጥንካሬ ማስኬድ ከተቻለ የጀግኖቻችንን መፈታት ብቻ ሳይሆን ከእንግዲህ ወዲያ ጀግኖች የማይታሰሩበት ስርዓት መፍጠር እንችላለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *