ዶ/ር አብይ አህመድ በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ክትትል እየተደረገበት ይገኛል

#ETHIOPIA | ዶ/ር አብይ አህመድ በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ክትትል እየተደረገበት ይገኛል

የጸጥታ ኃይሎች እና ማህበረሰብ (ESAT)

የኦህዴድ ም/ል ፕሬዝዳንትና የጽህፈት ቤቱ ዋና ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ በጌታቸው አሰፋ በሚመራው የደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ክትትል እየተደረገበት እንደሆነ ከደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። አቶ ጌታቸው አሰፋ በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ዶ/ር አብይ በሚያራምደው ሃሳብ ደስተኛ እንዳልሆነ ታውቋል። ይህን ተከትሎ በዶ/ር አብይ ላይ ክትትል እንዲደረግ ውሳኔ ተላልፎ የክትትል ተግባራት እየተፈፀመበት ይገኛል። በዚህ ሂደት ከዶ/ር አብይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ የቤተሰቡ አባላትም የክትትሉ ኢላማ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል። የዶ/ር አብይ ባለቤት ስልካቸው በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ስር በሚገኘው የቴክኒክ መረጃ ዋና መምሪያ ተጠልፎ ክትትል እየተደረገባት መሆኑ በደህንነት ዋና መስሪያ ቤት የሚሰሩ ወኪሎቻችን ያስረዳሉ። ዶ/ር አብይ ከመከላከያ ወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ጋር ቅርብ ግንኙነት አለው በሚል በአቶ ጌታቸው አሰፋ እንደሚጠረጠር ከጉዳዩ ጋር ቅርብ የሆኑ አካላት ይገልጻሉ። ዶ/ር አብይ አቶ ጌታቸው አሰፋ በተገኘበት የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ የጸጥታ ተቋማት የአሰራር ሂደት ደካማነትን በማጉላት መናገሩና እነዚህ ተቋማት ተቋማዊ ብቃትን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ እንደገና መቋቋም አለባቸው የሚለውን ሃሳብ ማስተጋባቱ አቶ ጌታቸው አሰፋን ክፉኛ አስቆጥቷል። ዶ/ር አብይ በስብሰባው ላይ በተደጋጋሚ እስካሁን በምንሄድበት መንገድ መሄድ አንችልም፤ ህዝቡ የሚፈልገውን ለውጥ እኛ መስጠት ካልቻልን የሁላችንንም መቃብር እራሳችን እየቆፈርን መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል በማለት ተናግሯል። ዶ/ር አብይ በኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ወቅቱን ያገናዘበ የለውጥ ሂደት ውስጥ መግባት አለብን በማለት ለማሳሰብ ቢሞክርም በተወሰኑ የህወሃት መሪዎች በኩል ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርበት ተስተውሏል። አቶ ጌታቸው አሰፋ ዶ/ር አብይ ከሚያነሳቸው ሃሳቦች ተቃራኒ የሆኑ ሃሳቦችን በማንሳት ተጽዕኖውን ለማሳረፍ ሲሞክር ተስተውሏል። አቶ ጌታቸው አሰፋ ቀን ከሚደረገው የኢህአዴግ ስብሰባ በኋላ ምሽት ላይ ከዶ/ር አብይና ከአቶ ለማ መገርሳ ጋር በመሆን ሲጨቃጨቁ እንደሚታዩ ከጉዳዩ ጋር ቅርብ የሆኑ አካላት ይገልጻሉ። ዶ/ር አብይ አቶ ጌታቸው አሰፋ በሚፈልገው መንገድ መሆን አለመቻሉ ከተወሰኑ የህወሃት አመራሮች ጋር ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ዶ/ር አብይ በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት የክትትል ራዳር ውስጥ እንዲገባ መደረጉ በአቶ ጌታቸው አሰፋ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚችል አቶ ጌታቸው አሰፋን በቅርብ የሚያውቁት አካላት ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። በደህንነቱ ውስጥ ያሉ ወኪሎቻችን እንደሚያስረዱት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚደረጉ ተቃውሞዎች የኦህዴድ እጅ አለበት የሚለው ምልከታ በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ገዢ ሃሳብ ሆኖ መውጣቱን ይናገራሉ። ይህን ተከትሎ እንደ ዶ/ር አብይ ያሉ የኦህዴድ ከፍተኛ ባለስልጣናትን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚደረገው ተቃውሞ ጋር በማያያዝ አቶ ጌታቸው አሰፋ እርምጃ ሊወስድባቸው ይችላል በማለት ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በዶ/ር አብይ ላይ በአሁን ሰአት እርምጃ የሚወሰድ ከሆነ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ አድማሱን እንዲያሰፋና በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል እንደሚያደርግ በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ የሚሰሩ ባለስልጣናት ጉዳዩን በአሳሳቢነቱ ማንሳታቸው ታውቋል። በመሆኑም ዶ/ር አቢይ ክትትል ቢደረግበትም ወዲያውኑ እርምጃ ሊወሰድበት እንደማይችል ፍንጭ ሰጥተዋል። ሆኖም በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት የሚሰሩ ወኪሎቻችን በዶ/ር አቢይ ላይ የሚያንዣብቡ አደጋዎች እንዳሉ ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም ዶ/ር አብይ ከኢንሳ ሃላፊነቱ የተነሳው በአቶ ጌታቸው አሰፋ ግፊት እንደሆነ ይታወሳል። ዶ/ር አብይ በመከላከያ ውስጥ ካሉ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ጋር ያለው መልካም ግንኙነት በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት በጥርጣሬ እንዲታይ አድርጐታል። ዶ/ር አብይ ከዚህ ቀደም በመከላከያ የወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ውስጥ ሲሰራ እንደነበር ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *