ኢሳት ዜና፣ ህዳር 29 ቀን 2010 ዓም )አርዱፍ ከህወሃት እና ከአፋር ልዩ ሃይል ጋር እየተዋጋ መሆኑን አስታወቀ

(ኢሳት ዜና፣ ህዳር 29 ቀን 2010 ዓም )አርዱፍ ከህወሃት እና ከአፋር ልዩ ሃይል ጋር እየተዋጋ መሆኑን አስታወቀ

የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራቲክ አንድነት ግንባር ለኢሳት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከህወሃት እና ከአፋር ልዩ ሃይል አባላት ጋር ሞጎሮሶ በተባለው ተራራ ላይ ለሳምንታት በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ዛሬም ቀጥሎአል።
የጥቃቱ አላማ አርዱፍን ከወታደራዊ ቤዙ ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ፣ አካባቢው ለቱሪስት እንቅስቃሴ አመቺ መሆኑን ለአውሮፓውያን ቱሪስቶች ለማሳየት፣ በሶማሊ ክልል እንደሚታየው ሁሉ በአንድ ጎሳ ላይ የተመሰረተ ልዩ ሃይል በአፋር ክልል የበላይነት እንዲኖረው ለማድረግ እንዲሁም በአፋር 6ኛ ዞን ለመመስረት በማሰብ የተደረገ መሆኑን መግለጫው ያትታል።
በአፋር ከሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች በአል ጋር በተያያዘ ከ580 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን የገለጸው አርዱፍ፣ ይህም በአካባቢው ህዝብ ላይ አለመረጋጋት እንደፈጠረ አስታውቋል።
ከህዳር መጨረሻ ጀምሮ በሞጎሮሶ ተራራ ላይ ሲካሄድ የቆየው ወታደራዊ ጥቃት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አርዱፍ የሚቆጣጠራቸውን ቦታዎች መልሶ ለመያዝ በተደረገ ሙከራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ድርጅቱ ገልጿል። ጥቃቶቹን ተከትሎ የህወሃት ወታደሮች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ መጡበት መመለሳቸውን ፣ 17 የህወሃት ወታደሮች መገደላቸውንና በርካቶች መቁሳላቸው ገልጿል። በአፋር ክልል ልዩ ሃይል ላይም ከፍተኛ የሆነ የሞራል ድቀት መድረሱን ወታደራዊ ድርጅቱ አመልክቷል።
አርዱፍ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ ወደዚህ አካባቢ መንቀሳቀስ እንደሌለበት ምክሩን ለግሷል። የውጭ አገር ኩባንያዎች፣ ጎብኝዎችና ባለህብቶች ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ አካባቢውን በፍጥነት ለቀው መውጣት አለባቸው ሲል የገለጸው አርዱፍ፣ የአፋር ልዩ ሃይል ልክ እንደ ሶማሊ ልዩ ሃይል ሁሉ በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ከክልል አልፎ ወደ አለማቀፍ ግጭት እየቀየረው ነው ሲል ድርጅቱ በመግለጫው ጠቅሷል።
አርዱፍ በመግለጫው በቅርቡ ህይወቱን ስላጣው ጀርመናዊ ቱሪስት የገለጸው ነገር የለም። መግለጫውን በተመለከተ በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በኩል የተሰጠ አስተያየት የለም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *