ብሔርተኞች እውነታውን ተጋፈጡት !!!

ብሔርተኞች እውነታውን ተጋፈጡት
‹‹ኤርሚያስ ቶኩማ››
በቅርቡ ብቅ ያሉት የአማራ ብሔርተኞች መቀስቀሻ በጣም ነው የሚያስቀኝ ሁሉም ለማለት በሚያስችል መልኩ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በማለታችን ነው የተጎዳነው” የሚል መፈክር በየስብሰባ አዳራሹ ሲያስተጋቡ እሰማለሁ ይቺ ነገር የኦሮሞ ብሔርተኞች “ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ውጤት ነች የኦሮሞ ህዝብ ተጨቁኗል መፍትሄው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ነው” ብለው በ1960ዎቹ የሰበኩት ስብከት ግልባጭ ነው። የኦሮሞ ብሔርተኞች ነፃ ኦሮሚያ ብለው በየስብሰባ አዳራሹ መጮህ ከጀመሩ 50 አመት ገደማ ቢሆናቸውም ቅርፃቸውን ቀይረው ከመጮህ ውጭ ለኦሮሞ ህዝብ የፈጠሩለት ምንም ነገር የለም ምክንያቱም እነርሱ ሲታገሉ የነበሩት መንፈስ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ማንነት እንጂ ፊዚካሊ መሬት ላይ የሚገኘውን ጨቋኝ ስርአት አልነበረም።
አሁንም በተመሳሳይ የአማራ ብሔርተኞች አማራ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በማለቱ ተጎዳ የሚል መፈክር አንግበው ተከታዮቻቸውን ለማብዛት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ እነርሱ ስለኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያ መጨነቅ እና ማውራት የጭቆና ምንጭ ነው ብለው ይሰብካሉ ይህ ደግሞ በእውነታው አለም ያለውን ሕወሃትን ከመፋለም ይልቅ በመንፈስ እና በሰዎች አስተሳሰብ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊነት ለመዋጋት እንዲነሳሱ ምክንያት ሆኗቸዋል አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ማለት ይሄ ነው፤ ጀግነህ መፋለም ካልቻልክ አማራ ነኝም አልክ ኢትዮጵያዊ በሕወሃት ከመገደል ልትተርፍ አትችልም። መጋፈጥ ካለብህ በመንፈስ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊነት ሣይሆን በአካል የሚገኘውን የአራት ኪሎውን መንግሥት ነው።
አንዳንዶች በአማራው ዘንድ የአማራ ብሔርተኝነት ማበብ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው ሲሉ እሰማለሁ ምን አይነት ለውጥ እንደመጣ ግን ሊገባኝ አልቻለም፤ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እራሳቸውን እንደአማራ ነፃ አውጪ የሚቆጥሩ ግለሰቦች በአማራው ስም የፖለቲካ ድርጅቶችን በመመስረት የገቢ ማሰባሰቢያና መግለጫ ከማውጣት ውጭ ቢያንስ ቢያንስ ነፃ እናወጣዋለን ብለው የሚያስቡት ህዝብ ልጆች በወያኔ እየተለቀሙ በየእስር ቤቱ ሲጣሉ ቤተሰቦቻቸውን እንኳን ሲረዱ አይታዩም ምን አልባት እዚህ ጋር ወያኔ መንገዱን ዘግቶ በየት በኩል ይርዱ ብላችሁ የምትጠይቁ ትኖራላቹህ አዎ ወያኔ መንገዱን ዘግቶታል ሆኖም ይህንን መንገድ አልፈው ለመሄድ አልያም ሌሎች አማራጭ መንገዶችን ለመጠቀም የሄዱበት ምንም አይነት መንገድ አላየሁም፡፡
በአሁኑ ወቅት ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ማውራት እንደነውረኝነትና አሳፋሪ ተግባር እየተቆጠረ ነው የሚገኘው በተቻለ መጠን ወጣቱ ጎሰኝነትን እንዲላበስ ብሎም ኢትዮጵያዊነትን እንዲጠየፍ ብሎም ስለኢትዮጵያ ማውራት አሳፋሪ ተግባር ሆኖ እየታየ ነው ሆኖም ነፃ አውጪ ነኝ ባዩም ሆነ ነፃ እወጣለሁ ብሎ የሚያስበው ግለሰብ ማፈር ያለበት በህወሃት በመገዛቱ እንጂ በኢትዮጵያዊነቱ ሊሆን አይገባም፤ እውነታውን መጋፈጥ አለባቸህ እየጨቆነህ ያለው ህወሃት እንጂ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ አይደለም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *