በሐፍረታቸው የሚኮሩ ብአዴኖች!

በሐፍረታቸው የሚኮሩ ብአዴኖች!

የላይ ጋይንት ወረዳ ብአዴኖች ሊያፍሩበት የሚገባቸውን ገመና በአደባባይ ሲመጻደቁበት አየሁ፤ አፈ ቀላጤያቸው እንዳለው ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ ነው ነገሩ፡፡ በዚህ መልኩ ስንት ዐማሮች በየቦታው እንደጠፉ እግዜር ይወቀው፡፡
መሠለ ጌታሁን የተባለ ጉብል የሃምሳ አለቃ ፍቅሬ አሉላን ልጅ ለማግባት ቀን ቆርጦ ድግስ እየተደገሰ ነበር፤ የሰርጉ ዕለት ጥር 7 ቀን 2009 ዓም ተወስኖ ለድግስ የሚሆን ቅቤ ከደብረ ታቦር ለመግዛት ሰርጉ 20 ቀናት ያክል ሲቀሩት ታኅሳስ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ከነፋስ መውጫ ተሳፈረ፡፡ ምስኪኑ ሙሽራ መሰለ ጌታሁን ግን ነገሮች በአሰበው መልኩ አልሔዱለትም፡፡
ደብረ ታቦር ሂዶ ቅቤ ለመግዛት ሲያማርጥ የትግሬ ደኅንነቶች መጥተው ይይዙታል፤ መታወቂያ ተጠይቆ ሲያሳይ ትውልድ ቦታው ኮምቦልቻ መኖሪያው ደግሞ ላይ ጋይንት ወረዳ መሆኑን አዩ፡፡ ለትግሬ ደኅንነት ዐማራ መሆን ብቻውን በቂ ቢሆንም ደብረ ታቦር አመጽ ለማስነሳት ተልከህ የመጣህ ነህ ብለው ከሃያ ሽህ ዐማሮች ጋር ወደ ብር ሸለቆ የቅጣት ቦታ ወሰዱት፡፡ ለነዚህ አረመኔዎች ሰርጌ በሦስት ሳምንት ውስጥ ነው፤ ሙሽሪት ትጠብቀኛለች የሚባል ነገር አያሳዝናቸውም፤ እንዲያውም ሰርጉን በማስተጓጎላቸው ደስታ ይሰማቸዋል!
የመሰለ ጓደኞች የገባበት ጠፋቸው፤ የሙሽሪት ቤተሰቦች ተጨነቁ፡፡ ለፖሊስ አመለከቱ፤ ጉዳዩን የያዘው የትግሬ ደኅንነት በመሆኑ የዐማራ ፖሊስ የማወቅ መብት አልነበረውም፡፡ በዚህ መካከል በላይ ጋይንት ወረዳ ቀበሌ 13 አንድ ምስኪን ዐማራ ተገድሎ ይገኛል፡፡ ብዙ ጊዜ በደኅንነት የሚገደሉ ሰዎች ማንነታቸው እንዳይታወቅ ተደርገው አካላቸው ይበላሻል፤ መታወቂያና ማንኛውም ዶክመት ይቃጠላል፤ ስለዚህ ይህ የማን እንደሆነ ያልታወቀ አስከሬንን ፖሊስ የመሰለ ጌታሁን ነው በሚል ለቤተሰቦቹ አስረከበ፡፡ ቤተሰብ አልቅሶ የካቲት 03 ቀበረ፡፡ በድፍን ጋይት እግዚኦ ተባለ፤ ገደ ቢስ ሙሽራ ተባለች ሙሽሪትም፡፡
ብር ሸለቆ ከ6 ወር በላይ ሲደበደብ የከረመው አቶ መሠለ ጌታሁን ከ6 ወራት የስቅይት ጊዜ በኋላ ነሐሴ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ከብር ሸለቆ ተለቀቀ፡፡ ሙቷል የተባለው ተዝካር የተበላበት ሰርጉ የተሰረዘው እሱም ከሕይወት መዝገብ ሕወሓት የሰረዘው ጌታሁን ጊዜ ሳያጠፋ ጋይንት ተከሰተ፡፡
የብአዴኖች ሐፍረተ ቢስ ሥራ አሁንም ይቀጥላል፤ መሠለ ጌታሁንን ወደ ብርሸለቆ የተወሰድኩት በሕገ ወጥ መሣሪያ ዝውውር ተከስሼ ነው በል፤ ይህን ካላልክ ግን መልሰን እናስርሃለን ይባላል፤ አለላቸውም፡፡
እንግዲህ ይህን የሚያሳፍር ዜና ነው የብአዴኖቹ ኮምዩኒኬሽን ጉዳይ ጽ/ቤት በኩራት የፖሊስን ጀብደኝነት ጠቅሶ የዘገበው፡፡ ቢያንስ እንኳ ተገድሎ የተገኘውን ሰው ማንነት መለት አልቻሉም፡፡
ማፈሪያዎች! ሙሉቀን ተስፋው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *