ጃሎ እንበል!!!!!

ጃሎ እንበል

ሞትን ያህል መከራ
ባሩድን ያህል መራራ
ጠጥቶ ሃገሩን ሊያኮራ
ቅንጣት ለነፍሱ ሳይፈራ
በሞቱ ታሪክ ሊሰራ
ይህ ነበር የጀግና ትውፊት ሃገር ትውልድን ያኮራ
………
የሃገሩን ሞት ሞቶ የራሱን ነፍስ ሊሰጣት
የፍቅሩን ፅናት ፈትኖ በባሩድ በእቶን እሳት
ጠላቱን አይቀጡ ቀጥቶ የክብሩን ፀዳል ሊያለብሳት
ዘጠኝ ሞት ከፊቱ ቀርቦ ጨልጦ ዘጠኝኑም ሞት
ዘጠኙም ሳይገለው ቀርቶ በሺህ ልብ ህይወት ዘርቶ
ከዘላለም እስከ ዘላለም ጥግ ህያው ታሪክ ዘርቶ
እንዲህ ነበር አባት ሲያልፍ አኩሪ ስራውን ተክቶ
…………..
ልጁም ያባቱን ወኔ ቆራጥ ተግባሩን ወርሶ
ለወገቡ ዘር መራራ ደሙን ከጀግና ልቡ ቀንሶ
እሱም ተክቶ ያልፋል ያገሩን ታሪክ አውርሶ
ይህ ነበር የኛ ታሪክ ድርሳኑን ላየው
ከግሉ ቅጦት ይልቅ ያገሩን ክብር ያሳየው
እንዲህ ለሀገር በመሞት ፈቃዷን እየፈፀምነ
ጎበዝ ሲያልፍ ጎበዝ ተክቶ ከዘንድሮ ላይ ደረስነ
……………
ዘንድሮስ! ዘንድሮስ! ዘንድሮማ ምን ይወራል
እድሜ ለስልጣኔ ለለጋ ህፃናት ይብላኝ ለአገራዊ ሁሉ መጥኔ
ልጄ ኑርልኝ ስትል ሃገር በብርክ ቆማ
የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ የእምዬን ተማፅኖ ላይሰማ
ወላጅ ለሞት ሲጣደፍ ጨቅላ ህፃናት በትኖ
እድሜ ባዛለው ጉልበቱ አያት ከልጅ ልጅ ታምኖ
አረጋዊነት ዘመኑ ማረፍ መጦሩ ቀረና
መውለድ እርግማን ሆነ ፀጋ መሆኑ አበቃና
………………..
ሌጣ ሆኖ እንደበቀለ ሳያስብ ለእናት አባቱ
ለግሉ ደስታ ሲማስ ሲታደፍ ለእሳት ጉልበቱ
ወላጁን በሃዘን ማግዶ ሲሰበር በለጋነቱ
ወዴት አቤት ይባላል መጥኔ ለዚያች እናቱ
የልጇን መረታት አይታ ሰፍሳፋ ልቧ ሲባባ
አንጀቷ ሁለት ተከፍሎ ፊቷ ሲታጠብ በእምባ
ላፍታ እንኳ ይህ ቢታወሰው ዘሎ ከእሳቱ ባልገባ
…………..
ጉድ ነው ጉድሽን ስሚ እማማ ከነእርምሽ መኖሩ ይብቃ
የጉድ ዘመን ትውልድሽ የአውሮፓ የላቲን መጢቃ
ክብሩን ሞራሉን ሸጦ እንኳን ለልጁ ሊተርፍ ለራሱም ገና ሳይበቃ
መች እንደአባቱ ሊያኖርሽ ለራሱም መኖር አቅቶት
20 30 ኬላውን አርባ መድፈን ተስኖት
በደዌ በትር ሲመታ ቡቃያው ጅምሩ ቀርቶ
ወፌ ቆመች እንዳላል የእምቦሳው ተስፋ ገርጥቶ
ጥናቱን ይስጥሽ እማማ አሳርሽ መከራሽ በዝቶ
እንደአሸን የፈላው ዘርሽ እንደአሸን ልርገፍ ካለ
ጎህ ሲቀድ የፈላው ዘርሽ ጀንበርን ማለፍ ካልቻለ
መገን ከማለት በቀር ከንግዲህ ሌላ ምን አ ለ
………………………………
ሽምግልና ላይገኝ ከእንግዲህ በተረት ይፃፍ
የእድሜ በረከት ስጦታው ሲዘጋ በደዌ ምዕራፍ
ጃሎ እንበል ጎበዝ እንፎክር የመኖር ገዳችን ቢመጣ
ወኔአችን ግሎ ተነስቶ ሞትን ካገሩ ሊያስወጣ
ያኔ ሃገር ስትጠራን በጭንቅ በጣር ተይዛ
ድረሱ አድኑኝ ስትል በጠላት አዝና ተክዛ
በቀረርቶ ፍርሃትን ገድለን በሽለላ ሞትን ደፍረን
የሀገርን መደፈር ላናይ በፈቃዳችን ሞተን
ታንኩን መትረየስ መድፉን ጎራዴን ታጥቀን ማርከናል
ጠላትን አይቀጡ ቀጥተን ወደመጣበት ልከናል
አንዴ አይደል ደርዘን ተዋግተን የወንዱን ሱሪ ፈተናል
ያኔም የነበር እኛ! አንሁን ያለን እኛ! እንዴት ያን ሁሉ ወኔ ለደዌ ሰተን እንተኛ
ጃሎ በል ጎበዝ እንፎክር የመኖር ገዳችን ይምጣ
ወኔአችን ግሎ ተነስቶ ሞትን ካገር ቢያስወጣ
ዱብ ዱብ ባይ እንደበረዶ በልጅነቱ በረሃ ለምዶ
እጥፍጥፍ እንደ ኩታ ልብስ አተኳኮሱ አንጀት የሚያርስ
እዚህ አጉርሶ እዚያ ቢልከው አንጀት ጉበቱን አዝለከለከው
ገና ወጣቱ የነበር ጣቱ
ያ ጎበዝ ጀግና ጠረፍ ነው ሞቱ
አትንኩኝ! አትንኩኝ! አትንኩኝ እያለ ታልፋለች ህይወቱ
አታታታታታታታታታታ እምምምምምምመምምምም……..

አበባው መላኩ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *