ኦሮሞ መርጃ ያዋጣችሁት ገንዘብ ለአምቦ ማረጂያ ሊውል እንደሚችልም በሃሳባችሁ ያዙት!

በኦህዴድ በኩል ገንዘብ ያዋጣችሁ ሰዎች ለሃረር ኦሮሞ መርጃ ያዋጣችሁት ገንዘብ ለአምቦ ማረጂያ ሊውል እንደሚችልም በሃሳባችሁ ያዙት!

…ሁለቱ ሰዎች በመግለጫቸው ላይ ያሉትን ሰማሁኝ… በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት አንዱ ፖለቲከኛ ሌላኛው ደግሞ ምንም ፖለቲካ አለማወቃቸው ነው። አቶ ለማ መገርሳ በጣም ጥንቃቄ በተሞላው መልኩ በርካታ ሺዎች የተፈናቀሉበትን ነውር ‘በአንዳንድ ግለሰቦች የተከናወነ ነው…’ ብለው ሲያድበሰብሱት አቶ አብዲ ኢሌ ግን ‘ይሄ ድርጊት ከአመራሮች ድጋፍ ውጪ ሊፈጸም አይችልም’ ከማለታቸውም በላይ፤ ከጅግጅጋ እና አካባቢው ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ እየተፈናቀሉ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለአወዳዩ ‘ጥቃት’ ምላሽ እንደሆነም በገደምዳሜ ተናግረዋል።

በዚህ መሃል ፌደራል መንግስቱ አፉን በሰም አሽጎ ዝም ብሏል። (ያለው ነገር ካለ ንገሩኝ) እንደኔ እምነት ለዚህ ወንጀል ግንባር ቀደም ተጠያቂዎቹ እነዚህ በፎቶግራፉ ላይ የሚገኙት ግለሰቦች ናቸው… ከዛም አለፍ ሲል አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ውስጥ የተቀመጠው መንግስት ተጠያቂ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በዚህ የንጹሃን ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀል ሳቢያ፤ ጃዋር መሃመድ እና ኦህዴድ በጋራ በመሆን ለወገን ገንዘብ እንሰብስብ ማለታቸውን አይተናል። እኔማ ጃዋር ገንዘብ ሲሰበስብ አይቼ በራሱ መንገድ ለተጎጂዎች ያድርሳል ብዬ አስቤ ነበር። (ኧረ ሼርም አድርጌው ነበር) አሁን ላይ ስመለከት ግን ወዳጃችን ጃዋር ሰዎች በኦሮሚያ ባንክ ገንዘብ እንዲያስገቡ ሁሉ እየቀሰቀሰ ነው። ያው የኔ ዘመዶች የዋሆች ስለሆኑ እና በጃዋር ላይ እምነት ስላላቸው እስካሁን በጎ ፈንድ ሚው ብቻ ከመቶ ሺህ ዶላር በላይ መሰብሰብ ችሏል። እኔ ገንዘብ ስብሰባው ሳይሆን የደነቀኝ ኦህዴድ ተጠያቂ በሆነበት ወንጀል ለራሱ ለኦህዴድ ገንዘብ መስጠት እንዴት ነው የሚያወጣው? የሚለው ነው…

ሲመስለኝ የጃዋር እና ኦህዴድ ህብረት የሚመነጨው የዚህ ሁሉ አድራጊ ህውሃት ነው እንጂ ኦህዴድ ከደሙ ንጹህ ነው ከሚል መነሻ ይመስለኛል። በሌሎቹም የተቃዋሚው ሰፈሮችም በተለይም ውጪ ሃገር በምንኖረው ላይ ተመሳሳይ ችግር አለ… ሁልግዜም ለበደሎች ሁሉ ህውሃትን ብቻ ነጥሎ ተጠያቂ ማድረግ ሌሎቹ ቅዱስ ናቸው ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል። በዚህ ድምዳሜ ይመስለኛል ዛሬ ጃዋር እና የኦሮሚያ ኮሚኒዩኬሽን ሚኒስቴር በተመሳሳይ ቋት ገንዘብ እናወጣ የሚሉት።

ሁልግዜም ቢሆን ለትክክለኛ ችግር ትክክለኛ ተጠያቂ ማድረግ ካልቻልን… ከማን ጋር ወዳጅ እንደምንሆን አናውቀውም!

ለማንኛውም በኦህዴድ በኩል ገንዘብ ያዋጣችሁ ሰዎች ለሃረር ኦሮሞ መርጃ ያዋጣችሁት ገንዘብ ለአምቦ ማረጂያ ሊውል እንደሚችልም በሃሳባችሁ ያዙት! አቤ ቶክቻው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *