ኢሳት ዜና } በምዕራብ ሀረርጌ መኢሶ ከተማ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ በተጣለው ቦምብ ሶስት ተማሪዎች መጎዳታቸው ተሰማ❗️

ኢሳት ዜና } በምዕራብ ሀረርጌ መኢሶ ከተማ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ በተጣለው ቦምብ ሶስት ተማሪዎች መጎዳታቸው ተሰማ❗️

ከቦምብ ጥቃቱ በኋላ በሶማሌ ልዩ ሃይል ታጣቂዎችና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል ውጊያ የተደረገ ሲሆን 6 ሰዎች መቁሰላቸውም ታውቋል። በውጊያው ከቆሰሉት መካከል ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ሰዎች ጭሮ ሆስፒታል መወሰዳቸው ታውቋል። ትላንት በመኢሶ በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል የተደረገው የሀገር ሽማግሌዎች ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነው የዛሬዎቹ ጥቃቶች የተሰነዘሩት። ከግጭቶቹ ጀርባ የመንግስት እጅ እንዳለበት መረጃዎች ያመለክታሉ። ትላንት በመኢሶ ከተማ የመኢሶ ወረዳ አስተዳደርና የመከላከያ ሰራዊት የቀጠናው ተወካዮች ያዘጋጁት ስብሰባ ለዛሬው የቦምብ ጥቃትና ይህንንም ተከትሎ ለተካሄደው ውጊያ መነሻ እንደሆነ ይነገራል። በትላንቱ ስብሰባ ከኦሮሞና ከሶማሌ የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች የተሳተፉ ሲሆን አወዛጋቢ ናቸው በሚል የሚነሱ አካባቢዎችን በተመለከተ የተዘጋጀው ካርታ ላይ ለመወያየት የተጠራ ስብሰባ እንደነበር የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ከአከባቢው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም ይህንን አረጋግጠዋል። በስብሰባ የቀረበው ካርታ በተለይ ለኦሮሞ ሽማግሌዎች የሚቀበሉት አልነበረም። አወዛጋቢ የተባሉት አካባቢዎች በካርታው ላይ በሶማሌ ክልል ስር ተጠቃለው የሚታዩ በመሆናቸው የኦሮሞ ሽማግሌዎች ስብሰባውን ረግጠው እንዲወጡ እንዳደረጋቸው ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው። ይህ ያለስምምነት የተቋረጠው ስብሰባ ለዛሬው ግጭትና የቦምብ ጥቃት ምክንያት መሆኑ እየተነገረ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከስብሰባው በኋላ ውጥረት የነገሰ ሲሆን የሶማሌ ልዩ ሃይል ጥቃት ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነበር። ይህ በዚህ ሁኔታ እያለ ነው በመኢሶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ የቦምብ ጥቃት የተፈጸመው። ሶስት ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ውጊያው በሶማሌ ልዩ ሃይል ታጣቂዎችና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል የተካሄደ እንደሆነ ቢገለጽም የኦሮሚያ ፈጥኖ ሃይል አባላት ሳይሳተፉ እንደልቀረም ይነገራል። የዕለቱ ውጊያ መኢሶ አቅራቢያ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የተካሄደ ሲሆን ለሰዓታት የዘለቀ ነው ተብሏል። በውጊያ ከኦሮሞ ተወላጆች በኩል ስድስት ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን የሁለቱ ከባድ በመሆኑ ወደ ጭሮ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የቦምቡ ፍንዳታ በተከሰተባት የመኢሶ ከተማ ውጥረቱ የበረታ እንደሆነ ማምሻውንም የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል። ጥቃቱ በሶማሌዎች በኩል እንደተፈጸ ቢገለጽም በኢሳት በኩል ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ሲቪል የለበሱ እንደሆኑ የሚገመቱ ሰዎች ቦምቡን ወርውረው ተሰውረዋል። ወዲያውኑ የመከላከያ ሰራዊት በስፍራው ደርሶ አካባቢውን የተቆጣጠረ ሲሆን በዙሪያው የተጀመረውንም ውጊያ ለማረጋጋት መሰማራታቸውም ታውቋል። ከአዋሽ የመጣው የመከላከያ ሰራዊት ከኦሮሚያ ፈጥኖ ፖሊሶችና ከህዝቡ ላይ መሳሪያ መንጠቁም እየተነገረ ነው። ይህም ለጥቃት የሚያጋልጠን ነው ሲሉ ነዋሪዎች በስጋት በመግለጽ ላይ ናቸው። በድንበር ይገባኛል ተጀመረ የተባለውና ዓመታት ያስቆጠረው ፍጥጫ በየዕለቱ የንጹሃንን ህይወት በማጥፋት ላይ ይገኛል። ከሁለቱም ወገኖች እንደሚገለጸው ለዚህ ደም አፋሳሽ ግጭት ዋነኛ ተጠያቂ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ነው። በጀርባ ካራ ለሁለቱም ወገኖች የሚያቀብለው የህወሀት መንግስት ነው የሚለው ሀሳብ ሁሉንም ወገኖች የሚያስማማ ሆኗል። የመኢሶ ነዋሪዎችም ይህንን ይገልጻሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *