ጋምቢያዊው› ምኒልክ!

‹ጋምቢያዊው› ምኒልክ!

ባለፈው ሳምንት እዚህ እምኖርበት አገር ከተለያየ ቦታ ከመጡ ሰዎች ጋር የቡድን ጨዋታ የምንጫወትበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የጨዋታው አሸናፊ በቡድን ሲሆን እኔና ቀጥዬ ታሪኩን ምነግራችሁ ልጅ ብቻ ነበርን አፍሪካውያን፡፡
ልጁ ኢትዮጵያዊ መሆኔን ወዲያው ነበር ያወቀኝ፡፡ ስም ስንለዋወጥ ‹‹ምኒልክ›› ሲለኝ ፊቷ በደስታ እንደዚያች ቀን የፈካበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ ልጅ ጋምቢያዊ ነው፡፡ ቡድን ስንመራረጥ እኔና እሱ በአንድ ቡድን ሆንን፡፡ በኋላ የቡድናችሁን ስያሜ ስጡት ስንባል ምኒልክ ከሁሉም ቀድሞ የእኛን ቡድን ‹‹አድዋ›› አለው፤ ነጮች ብቻ ያሉበት ቡድን ደግሞ ‹‹ታሊን›› ተብሎ ጨዋታው ተጀመረ፡፡
ምኒልክ ቡድናችን ለምን አድዋ እንዳለው ከራሱ ስም ጋር እያገናኘ ሲያብራራ የምር ነው የምላችሁ የእምዬ ምኒልክን ኃያልነት እንደዚያ ቀን ገብቶኝ አያውቅም ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ታዲያ ይኼው ልጅ በጨዋታውም የተካነ ነበርና ጨዋታውን በእርሱ ብርታት አሸነፍን፡፡
ምናልባት ሲጫወቱ የነበሩት ነጮች እኛ ያወራነው ትርጉም ላይሰጣቸው ይችላል፤ ሆኖም ለመላው ጥቁር ሕዝብ ምኒልክ የቱን ያክል ኩራትና ክብር መሆኑን ግን የተረዳሁበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓም በአንጎላላ የተወለዱትን እምዬ ምኒልክ በተመለከተ በርካታ የውጭና የእኛ አገር ጸሐፍት ብዙ ከትበዋል፡፡ ንግሥ ሳህለ ሥላሴ ‹‹ምኒልክ የሚባል ንጉሥ ዓለምን ይገዛል›› የሚለውን ትንቢት ይዘው ‹‹እኔ ነኝ ምኒልክ›› ይሉ ነበር አሉ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን በሕልማቸው ከልጃቸው ልጅ ጋር ቆመው ሳለ የሕፃኑ ጥላ የእሳቸውን ጥላ ብዙ በለጠው፡፡ ከዚያም ምኒልክ የልጃቸው ልጅ እንደሆነ ተገነዘቡ ይላሉ አለቃ ለማ ኃይሉ (ልጃቸው መንግሥቱ ለማ ‹‹መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ›› ብለው ባሳተሙት መጽሐፍ)፡፡ አለቃ ለማ ስለ እምዬ ምኒልክ ውልደት እና ስያሜ የሚጣፍጥ ታሪክ ነግረውን አልፈዋል፤ ሙሉውን ታሪክ አንብቡት፡፡
እንደተባለው በዓለም ታሪክ በጥቁር ሰው ዘር እንደ እምየ ምኒልክ የታፈረና የተከበረ መሪ ዓለማችን እስካሁን አላፈራችም፡፡ እኛ ጥቁር አፍሪካውያን በታሪክ አኩርቶንና አስከብሮን ያለፈ ከእምዬ ምኒልክ የላቀ መሪ ኖሮን አያውቅም ማለት ይቻላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *