አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ አምስት አምባሳደሮች ወደ ሀገር ቤት መጠራታቸው ተዘገበ!!!!!

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 8/2009)አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ አምስት አምባሳደሮች ወደ ሀገር ቤት መጠራታቸው ተዘገበ። በተጠሩት አምባሳደሮች ምትክ አዳዲስ ግለሰቦች እንደሚሾሙም ተመልክቷል። በማይታወቅ የገንዘብ ምንጭ በተለያዩ የንግድ ተቋማት ውስጥ ባለድርሻ መሆናቸው የሚገለጸው አምባሳደር ግርማ ብሩ የጸረ መስናው ዘመቻ እስኪያቆም በሕክምና አሳበው ሊዘገዩ እንደሚችሉም የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ። በዩ ኤስ አሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሆኑት ከአቶ ግርማ ብሩ በተጨማሪ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ስዩም መስፍን በተመሳሳይ ወደ አዲስ አበባ ተጠርተዋል። ሪፖርተር የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሁለቱ ነባር የኢህአዴግ አባላት በተጨማሪ በቤልጂየም፣በፈረንሳይና በአየርላንድ በአምባሳደርነት የሚያገለግሉት አቶ ተሾመ ቶጋ፣አቶ ነጋ ጸጋዬና አቶ ሬድዋን ሁሴን በተመሳሳይ ወደ ሀገር ቤት ተጠርተዋል። የተጠሩትን አምባሳደሮች የሚተኩ ሌሎች አምባሳደሮች ሐምሌ 19/2009 መመረጣቸውና መሾማቸውም ይታወሳል። ላለፉት 6 አመታት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩትን የሕወሃቱን አቶ ስዩም መስፍንን የሚተኩት ሌላው የሕወሃት ታጋይ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ መሆናቸውን የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ። ላለፉት 26 አመታት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደርነት ቦታን ከሕወሃት ሰዎች ውጪ ለሌሎች የማይሰጥበት ምክንያት እንቆቅልሽ ሆኖ ቀጥሏል። ከአቶ ስዩም መስፍን በፊት የሕዋሃቶቹ አቶ ሃይለኪሮስ ገሰሰ ነበሩ።ከርሳቸው በፊት ደግሞ ዶክተር አዲስአለም ባሌማ በአምባሳደርነት ቆይተዋል። በዩ ኤስ አሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግርማ ብሩን የሚተኩት የብአዴኑ አቶ ካሳ ተክለብርሃን መሆናቸውን የሚገልጹት ምንጮች የተነሱት አምባሳደሮች ወዴት እንደሚወሰዱ በዝርዝር ያስታወቁት ነገር የለም።ነገር ግን በሚኒስትር ደረጃ የሚሾሙ እንደሚኖሩ ሳይጠቁሙ አላለፉም። ከፈረንሳይ ፣ቤልጂየምና አየርላንድ የተነሱት አቶ ተሾመ ቶጋ፣አቶ ነጋ ጸጋዬና አቶ ሬድዋን ሁሴን በመጪው ጥቅምት የሚኒስትርነት ቦታ እንደሚሰጣቸው ሲገመት አቶ ስዩም መስፍን ከጤና ጋር ተያይዞ በጡረታ እንደሚገለሉ ይጠበቃል። አምባሳደር ግርማ ብሩ በአቶ አባይ ጸሃዬ ወደሚመራው የፖሊሲ ምርምርና ጥናት ተቋም ውስጥ ይመደባሉ የሚል እምነት እንዳለም መረጃው አመልክቷል። አሁን በሙስና ስም ተጠርጣሪ ሌቦችን የማሰሩ ርምጃ ከቀጠለ ከልዩ ልዩ ተቋማት፣ፋብሪካዎችና ህንጻዎች ጋር በተያያዘ ስማቸው የሚነሳው አቶ ግርማ ብሩ ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸው አጠራጣሪ ሆኗል። ሁኔታዎች እስኪረጋጉ በሕክምና ሰበብ አሜሪካ ሊቆዩ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *