ዶ/ር መረራን ጨምሮ ሌሎች ምሁራንን ከዩኒቨርሲቲ ያባረሩት ግለሰብ ሹመት ተሰጣቸው

ዶ/ር መረራን ጨምሮ ሌሎች ምሁራንን ከዩኒቨርሲቲ ያባረሩት ግለሰብ ሹመት ተሰጣቸው

BBN news July 27, 2017
ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ሌሎች ምሁራንን ከዩኒቨርሲቲ ያባረሩት ግለሰብ ሹመት ተሰጣቸው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዲን የነበሩት ፕ/ር አድማሱ ጸጋዬ፣ ዩኒቨርሲቲውን በሚመሩበት ወቅት ዶ/ር መረራን ጨምሮ ሌሎች በስርዓቱ ላይ ትችት የሚያቀርቡ ምሁራንን ሲያባርሩ ቆይተዋል፡፡ ግለሰቡ በመጨረሻም ባገለገሉት ህወሓት አማካይነት የአምባሳደርነት ሹመት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ አማካይነት ተሰጠ በተባለው በዚህ የአምባሳደርነት ሹመት ውስጥ ስማቸው ከተካተቱ የስርዓቱ ሰዎች መካከል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በዲንነት ሲመሩ የነበሩት ፕ/ር አድማሱ ጸጋዬ ይገኙበታል፡፡
ግለሰቡ በህወሓት አማካይነት ወደ ዩኒቨርሲቲው ከመጡ ወዲህ፣ ግቢውን በፖለቲካ ምስቅልቅሉን አውጥተውታል ተብለው ይታማሉ፡፡ በእሳቸው ዘመን ለዘመናት ካስተማሩበት ዩኒቨርሲቲ ከተባረሩት ምሁራን መካከል ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ፕ/ር አድማሱ ጸጋዬ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው እና በተማሪዎቻቸው ዘንድ ክብር ያላቸውን ምሁራን በብጣሽ ወረቀት ሲያባርሩ ከርመው፣ በመጨረሻም ኢትዮጵያን በውጭ ሀገር ከሚወክሉ አምባሳደሮች ተርታ ተሰልፈዋል፡፡
ራሱ ህወሓት ባወጣው ህግ ዩኒቨርሲቲዎች ከማንኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የጸዱ ናቸው የሚል ነገር ቢሰፍርም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዲን የነበሩት ግለሰብ ግን፣ በህወሓት ትዕዛዝ ምሁራንን ከዩኒቨርሲቲ ሲያባርሩ እና ሲያስባርሩ ቆይተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ቤተ ህወሓት በማድረግም የተለያዩ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ሲያስተላልፉ መቆየታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በፖለቲካ አመለካከት ከህወሓት የተለዩ ተማሪዎችን በማባረርም ለስርዓቱ ውለታ ሲውሉ የቆዩት ፕ/ር አድማሱ ጸጋዬ፣ የዩኒቨርሲቲው ዲን ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ህወሓትን ሲያገልግሉ ቆይተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *