ደርግ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፣ እኔ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ!”ህወኃት

“ ደርግ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፣ እኔ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ!”ህወኃት
ደረጀ ሀ.

እስራኤልም ሁሉ መጥተው ሮብዓምን፦“አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቅልልልን፥ እኛም እንገዛልሃለን” ብለው ተናገሩት።
እርሱም፦”ከሦስት ቀን በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ” አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።
ንጉሡም ሮብዓም፦ “ ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው?” ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ።
እነርሱም፦ “ለዚህ ሕዝብ ቸርነት ብታደርግላቸው፥ ደስም ብታሰኛቸው፥ በገርነትም ብትናገራቸው፥ ለዘላለም ባሪያዎች ይሆኑልሃል” ብለው ተናገሩት።
እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ነገር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ።
(ልክ አሁን ያለው ጉጅሌ አገዛዝ ፣ ለሆዳቸው ያደሩ ኅሊና ቢስ ምናምንቴ ጎረምሳዎችን “አማካሪ” እያለ እንደሚሰበስበው ማለት ነው። )
ንጉሥ ሮብዓም ፦”አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው አላቸው ምናምንቴዎቹን።
ምናምንቴዎቹም ምክራቸውን እንደሚከተለው ሰጡት፦

“አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፥ አንተ ግን አቅልልልን ለሚሉህ ሕዝብ። ታናሽቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው” ብለው ተናገሩት።
(ልክ ዛሬ ሕዝብ ብሶቱ በዝቶበት አቤቱታና ጥያቄ ሲያቀርብ “እባክህ መንግስታችን የሕዝቡን ድምስ ስማ?” በማለት ፋንታ ፦” ይሄማ ሽብርተኝነት ነው፣ መንግስት በነውጠኞች ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት! እስከመቼ ነው ዝም የሚለው? በለው፣ ፍለጠው!” እያሉ በንዴት እንደሚንጫጩት ኮተታም ካድሬዎች ማለት ነው)

ንጉሡ በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ ብሎ እንደ ተናገረ ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ።
ጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፦
“አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን እጨምርበታለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ ብሎ” እንደ ምናምንቴዎቹ ምክር ተናገራቸው። አደረገባቸውም።
(ልክ ጉጅሌው አገዛዝ በምናምንቴ የጎረምሳ አማካሪዎቹ አንዴ የሽብርተኝነት ህግ፣ አንዴ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር የወጣ ህግ፣ አንዴ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ አንዴ የግብር አዋጅ… እያለ ሕዝቡን በአፋኝ አዋጆችና ቀንበሮች ተጭኖ እያስለቀሰ እንደሚገኝ ማለት ነው)
(ያኔ ሕዝብ ሮብዓምን ፦”የአባትህን ቀንበር አቅልልልን” ብሎ ሲጠይቀው “ አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፣ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ!” እንዳላቸውም፤ እነሆ ጉጅሌውም ፦”የደርግን ቀንበር አቅልልልን?” ብሎ የጠየቀውን ሕዝብ ፦”ደርግ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፣ እኔ ግን ብረጊንጥ እገርፋችኋለሁ!”እያለውና እያስለቀሰው ይገኛል።)

ሕዝቡም ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ፦”በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? ከእንግዲህ በእሴይ ልጅ ዘንድ ርስት የለንም”ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እስራኤልም ሁሉ ወደየድንኳኖቻቸው ሄዱ። አኮረፉ።
ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶራምን ሰደደ፤ የእስራኤልም ልጆች በድንጋይ ወገሩት፥ ሞተም።
(አልሰማ ያለው ንጉሥ አስገባሪ ሲልክበት ሕዝብ አልገብርም አለ።ይልቁንም አስገባሪውን በድንጋይ ወገሩት። ዛሬ አልሰማና አላመዛዝን ያለ ጉጅሌ መንግስት የሕዝብን አቅም ያላገነዘበ ብቻ ሳይሆን ሕዝብን የሚገድል ግብር በመጫኑ ምክንያት ሕዝቡ አልገብርም ብሎ ማመጹ አይገርምም። አንዳንዶች አልገብርም ከማለት አልፈውም ቁጣቸውን በተለያዩ መንገድ እስከ መግለጽ መጀመራቸው አይደንቅም። ቀንበሩ የከበደው ሰው ከዚህም በላይ ሊያደርግ ይችላል።)
በስተመጨረሻም የአስገባሪዎቹን መገደል የሰማው ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሰረገላው ወጣ። ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ። እስራኤልም ከንጉሡ ቤት ሸፈተ።
( በጎ ምክርን ያልሰማ ንጉሥ መጨረሻው ይኸው ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ከጉጅሌው አገዛዝ ከሸፈተ ቆይቷል:ብርሌ ከነቃ አይሆንም ዕቃ” እንዲሉ ልቡ የሸፈተን ሕዝብ በምንም ዓይነት መደለያም ሆነ በማናቸውም ኃይል መግዛት አይቻልም። ቀንበርን በማክበድና በጊንጥ በመግረፍ(ኃይልን በመጠቀም) አገዛዝን ለማጽናት መፍጨርጨር መጨረሻው ውርደት መሆኑን አስረግጠን እንናገራለን።)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *