መኖር ማለት ማግኘት አይደለም፤ መኖር ማለት መትረፍረፍ አይደለም፤ መክበር እና መንፈላሰስ አይደለምመኖር ማለት ማሰብ ነው በሥጋ ሳይሆን በኅሊናህ ኑር በኅሊናህ ከኖርክ የተዘጋ መንገድ የለምቢኖርም ትከፍተዋለህ!!!!!!

ኅሊና እና መንገድ
( ዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

አንድ ሰው ከሚያሳድዱት ሰዎች እየሸሸ ይሮጣል፡፡ ሊያመልጥ በሚችልባቸው መንገዶች ሁሉ እየተሹሎከሎከ ተጓዘ፡፡ ሰዎቹ እንዳያዩት ሊደበቅባቸው በሚችሉ አማራጮች ሁሉ ተፈተለከ፡፡ በስተ መጨረሻ እግሩ ከአንድ ግምብ አጠገብ አደረሰው፡፡ ግንቡ እጅግ ቁመታም እና ረዥም ነበር፡፡ ተንጠላጥሎ ለማለፍም ምንም ዓይነት መወጣጫ አልነበረውም፡፡ ምናልባት የሚያስገባ ቀዳዳ ባገኝ ብሎ የግንቡን ጥግ ተከትሎ ሮጠ፡፡ ነገር ግን እርሱ ደከመው እንጂ መገቢያ ሊያገኝ አለቻለም፡፡

በመጨረሻ ተስፋ ሊቆርጥ ደረሰ፡፡ ከኋላው የሚያሳደዱት ሰዎች እንደርሱው ግንቡን ሲያዩ መጀመርያ ደነገጡ፤ በኋላ ግን እርሱን ለመያዝ አመቺ መሆኑን ዐውቀው ደስ አላቸው፡፡ ሊሄድ ይችላል በሚሏቸው በሁለቱ የግንቡ አቅጣጫዎች ተከፋፍለው ሮጡ ፡፡

ልቡ እየደከመ፣ ሃሳቡ እየዛለ፣ እንጥሉ እየወረደ፣ ሐሞቱ እየፈሰሰ፣ አንጅቱ እየራቀ፣ መቅኔው እያለቀ መጣ፡፡ «ይህንን ሁሉ መንገድ ለፍቼ ለፍቼ ሊይዙኝ ነው» ብሎም ከአንድ ዛፍ ሥር ቁጭ ብሎ አለቀሰ፡፡ ዕንባውን ጠርጎ ቀና ሲል ከግንቡ ራቅ ካለ ዛፍ ላይ የተጠጋ አንድ ሐረግ አየ፡፡ የሐረጉን ሥር በዓይኑ ሲከተለው ከግንቡ በላይ ከወጣው ዛፍ ተንጠላጥሎ ሲሳብ አየው፡፡ ጥቂት ብርታት አገኘ፡፡ ተስፋ ካለ ብርታት አለና፡፡ ሰው የሚደክመው ኅሊናው ሲደክም ነው፡፡

ጠጋ ብሎ ሐረጉን ያስጠጋውን ዛፍ ተደገፈ፡፡ ጠንካራ ነው፡፡ «ምን ላድርግ?» አለና ተጨነቀ፡፡ ያለ የሌለ ዐቅሙን አሟጠጠ እና ዛፉ ላይ ወጣ፡፡ የሐረጉንም ጫፍ ሳብ ሳብ አደረገው፡፡ ጠንካራ ነው፡፡ መልሶ መላልሶ ሳበው፤ ሐረጉ ጠንካራ ነው፡፡ ይህን ጊዜ የሰው ድምጽ ሰማ፡፡ ዝቅ ብሎ ሲያይ የሚያሳድዱት ሰዎች በአካባቢው ደርሰዋል፡፡ ደግነቱ አላዩትም፡፡

ሐረጉን በመዳፉ ጠመጠመና ወደ ኋላ ተስቦ ዛፉን በኃይል ለቀቀው፡፡ ያን ጊዜ ሐረጉ እንደ ፔንዱለም ተወርውሮ ከግንቡ በላይ አንጠለጠለው፡፡ ቋ ቋ ቋ የሚል ድምጽ ሰማና ሐረጉ ተበጠሰበት፡፡ ደግነቱ የወደቀው ግንቡ ላይ ነበር፡፡ ዘወር ሲል አሳዳጆቹ አይተውታል፡፡ የተረፈችውን ሐረግ ይዞ ወደ ምድር ወረደ፡፡

ክዚያ በኋላ የሆነውን አያውቀውም፡፡ ሮጠ ሮጠ ሮጠ እናም በቃ ሮጠ፡፡ ሲበቃው ዐረፈ፡፡ ሰውነቱ እንጂ ኅሊናው አላረፈም ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ አንዳች ማምለጫ ለምን አላገኘሁም፡፡ ይህንን ሁሉ ስደክም ያለተገለጠልኝ መንገድ እንዴት አሁን ታየኝ? ያወጣ ያወርድ ጀመር፡፡

እናም መንፈስ እንዲህ አለው፡፡ መጀመርያኮ ትሮጥ የነበረው በኅሊናህ አይደለም በእግርህ ብቻ ነው፡፡ እግርህ መሄድ ስለቻለ እና መንገዱም ሊያስኬድህ ስለቻለ ብቻ ነው የሮጥከው፡፡ ስለቻሉ መሮጥ አና እንዲችሉ ሆኖ መሮጥ ይለያያሉ፡፡ ስለሚያስኬድ መሄድ እና እንዲያስኬድ ሆኖ መሄድ ይለያያሉ፡፡» አለው፡፡ ይኼኔ ሰውዬው ደንግጦ «እንዴት?» አለ፡፡

አንዳንድ ጊዜ አጋጣሚዎች፣ ሁኔታዎች እና መንገዶች ይመቻቹልሃል፡፡ ያንተ ሃሳብ ሳይጨመርበት እንዲሁ የሚያፈራ ፍሬ፣ የሚወጣ እንጀራ፣ የሚያተርፍ ንግድ፣ የሚያበላ ሥልጣን፣ እና የሚያስደስት ትዳር ይገጥምሃል፡፡ ይኼኔ ኅሊናህ ቦዘኔ ይሆናል፡፡ መሄድህን እንጂ መድረሻህን አታውቀውም፡፡

እንዲህ የሆኑ ሰዎች እንዳንተ የተዘጋ የመሰለ ግንብ ሲገጥማቸው ይደነግጣሉ፡፡ ቦዘኔ የነበረ ኅሊናቸውን ቀስቅሰው ማሠራት ይከብዳቸዋል፡፡ ቦዘኔ ኅሊናን ከመቀስቀስ ደግሞ የሞተ የመኪና ባትሪ መቀስቀስ ይሻላል፡፡

አጋጣሚኮ መነሻ እንጂ መድረሻ መሆን የለበትም፡፡ የበረደን የመኪና ሞተር በባትሪ እንደ ሚያስነሡት የተኛን ኅሊና በአጋጣሚዎች ሊቀሰቅሱት ይቻላል፡፡ መኪናን በባትሪ ኃይል አይነዱትም፡፡ ሕይወትንም በአጋጣሚ አይመሯትም፡፡

አንድ ነጋዴኮ በአጋጣሚ ጥሩ ቦታ ላይ ስላለ፣ ዕድለኛም ስለሆነ፣ ብቸኛም ስለሆነ፣ ጊዜውም ስለረዳው፣ ሊበለጽግ ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን የኅሊናን ርዳታ ሳይፈልጉ እንደ አንተ እግር የሚኳትኑ ናቸው፡፡ አንተኮ ለጊዜው አምልጠሃል፤ ሸሽተሃል፤ መፍትሔ አግኝተሃል፡፡ ነገር ግን ኅሊናን የሚጠይቅ ጊዜ ላይ ስትደርስ ነበር የተሸነፍከው፡፡ ያም ነጋዴ ኅሊናን የሚጠይቅ አንድ ቀን ያጋጥመዋል፡፡ ዕድል ተበላሽቶ፣ ዘመን ተቀይሮ፣ ባለ ሥልጣን ወርዶ፣ ኑሮ ተለውጦ፣ ቦታውንም ተቀምቶ፣ ተወዳዳሪም በዝቶ ያ እንደ ልቡ የሚሮጥበት መንገድ የተዘጋ ሊመስለው ይችላል፡፡

ታድያ ያን ጊዜ ተኝቶ የኖረን ቦዘኔ ኅሊና መቀስቀስ ከባድ ነው፡፡

በጣልያን ጊዜ ከጣልያን ጋር አብረው ሕዝባቸውን እየወጉ በዘመኑ የሚጠቀሙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ዘመኑ የሰጣቸውን ከመብላት፣ ከመጠጣት፣ ከመሾም፣ ከማጋበስ፣ ከመላላክ፣ በቀር ኅሊናቸውን ያልተጠቀሙ፡፡ ቦዘኔ ኅሊና የነበራቸው ሰዎች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አጋጣሚውን ዕውቀት ለመቅሰም፣ ሥልጣኔን ለመማር፣ ሞያ ለመልመድ የተጠቀሙበት ባለ ኅሊናዎችም ነበሩ፡፡ በአንድ በኩል ከጣልያን የሚያስቀሩትን እያስቀሩ በሌላ በኩል የውስጥ አርበኞች ሆነው የሠሩ ንቁ ኅሊና ያላቸው ሰዎች ነበሩ፡፡

ታድያ ሕዝቡ በእነዚያ ቦዘኔ ኅሊና ባላቸው ሰዎች በማዘኑ የተነሣ

አርኩም ይሄድና

ሶልዲውም ያልቅና

ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና

ብሎ ገጠመ ይባላል፡፡ ብዙዎቹ አስበውበት አልነበረም የኖሩት፤ እንዴው ዘመን የወደደውን፣ ጊዜ የወለደውን ሲያደርጉ እንጂ፡፡ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብለው እንጂ፡፡ ታድያ በኋላ ተቸገሩ፡፡ አርኩም ሄደና ሶልዲውም አለቀና ተቸገሩ፡፡ የቦዘነ ኅሊናቸውን ተነሥ ቢሉት እምቢ አላቸው፡፡ ትርፍራፊ እና ልቅምቃሚ ለምዶ፣ ችሮታ እና ስጦታ ለምዶ አሁን ምን ይዋጠው፡፡

አየህ ምግብ ቀረበ ተብሎ ያለ አሳብ አይበላም፣ አልጋ ተመቸ ተብሎ ያለ አሳብ አይተኛም፡፡ ጨዋታ ደራ ተብሎ ያለ ልክ አይወራም፤ ገንዘብ አለ ተብሎ ያለ መጠን አይወጣም፤ እግር አለ ተብሎ ያለ ምዕራፍ አይኬድም፡፡ ይህ ኅሊናን ማቦዘን ነው፡፡

ለመሆኑ ለምን ነበር ያ ሐረግ የታየህ?

አማራጭ አልነበረህም፡፡ አሁን እግር እንደወሰደ የሚኬድበት መንገድ የለም፡፡ ያለው ግንቡ ብቻ ነው፡፡ የግድ ኅሊናህ መሥራት ነበረበት፡፡ አሁን አጋጣሚዎች አያጋጥሙህም አጋጣሚ ትፈጥራለህ እንጂ፤ መንገድህ አልቋል መንገድ ታበጃለህ እንጂ፡፡ ስለዚህ ኅሊናህ በውጥረት መሥራት ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ ሐረጉን አየኸው፡፡

ማየት አቅቶህ እንጂ እዚህ ድረስ ሳትደክም ልታመልጥባቸው የምትችል አያሌ መንገዶች ነበሩህ፡፡ አንተ ግን ኅሊናህን ስላቦዘንከው ልታያቸው አልቻልክም፡፡ እንዲሁ እግርህ እንደሄደልህ፣ መንገድ እንደወሰደህ፣ አገር እንደ ቀናህ ነበር የምትሮጠው፡፡ ታድያ እንዴት ታየው?

ዝግ ኅሊና እንጂ ዝግ መንገድ የለም፡፡

መንገድ የሚከፈተው ኅሊናህ ውስጥ ነው፡፡ አስቀድመው በኅሊና መንገድ ወደ ጨረቃ የሄዱ ሰዎች በኋላ በመንኮራኩር መንገድ ለመሄድ አልቸገራቸውም፡፡ የኅሊናቸው መንገድ ዝግ የሆነባቸው ግን ይኼው አሁንም «ጨረቃ ድንቡል ቦቃ ዐጤ ቤት ገባች ዐውቃ» እያሉ በመዝፈን ላይ ናቸው፡፡

ማጂላን ዓለምን ከመዞሩ በፊት ኅሊናው ዓለምን ዞሮ ነበር፤ ቫስኮ ዳጋማ ሕንድ ከመድረሱ በፊት ኅሊናው ደርሶ ነበር፡፡ ዋናው ኅሊና ነው፡፡ አስቀድሞ ኅሊናቸው የጸደቀ ሰዎች እኮ ናቸው በኋላም አካላቸው የሚጸድቀው፡፡

መኖር ማለት ማግኘት አይደለም፤ መኖር ማለት መትረፍረፍ አይደለም፤ መክበር እና መንፈላሰስ አይደለም፡፡ መኖር ማለት ማሰብ ነው፡፡ በሥጋ ሳይሆን በኅሊናህ ኑር፡፡ በኅሊናህ ከኖርክ የተዘጋ መንገድ የለም፡፡ ቢኖርም ትከፍተዋለህ፡፡

አንድ ታሪክ ልንገርህ፡

አንድ ፈላስፋ ነበር አሉ፡፡ አንድ ቀን መንገድ ሲሄድ መሸበትና ከአንድ ዛፍ ሥር ዐረፍ አለ፡፡ ጨለማው እንደ ግብጽ ጨለማ የተጠቀጠቀ ነበር፡፡ ፈላስፋው ምናልባት አንዳች ነገር በዚህ ጨለማ ውስጥ ብመለከት አለና ዓይኑን ፍጥጥ አድርጎ ማየት ጀመረ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ዓይኑን ደከመው፡፡ እየጨፈነ እና እየገለጠ ማየት ቀጠለ፡፡ ትንሽ ቆይቶ የሆነ የብርሃን ጭላንጭል ታየው፡፡ እየቆየ ሲሄድ አካባቢውን በደምሳሳው ማየት ቻለ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ከፊት ለፊቱ ያለው የበቆሎ እርሻ መሆኑን ለየ፡፡ በመጨረሻም በእርሱ እና በበቆሎ እርሻው መካከል የጥበቃ ማማ ታየው፡፡

ወዲያው አፈፍ አለና ተነሣ፡፡ ወደ ማማው ሄዶ በዚያ አደረ፡፡ በአውሬ ከመበላትም ዳነ፡፡ ይህ ፈላስፋ ታድያ ምን አለ መሰለህ «ማየት ለሚችል ሰው በጨለማ ውስጥ ብርሃን አለ፡፡ ጨለማን ጨለማ ያደረገው የፀሐይ መጥፋት ሳይሆን የኛ አለማየት ነው» አለ፡፡

እኔስ የኅሊና እንጂ የመንገድ ዝግ የለውም ያልኩህ ይህንኑ አይደል?

ይህንን ነግሮት መንፈሱ ከእርሱ ተለየ፡፡ መንገደኛውም የመንፈሱን ትሩፋት ተቀብሎ ሄደ፡፡ ይህንን ከወሬ ወሬ የሰማ አንድ ሰውም እነሆ በብሎጉ ላይ ጻፈው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *