ጋሹ እንዴት እንደተሰደደ? ከበውቀቱ ስዮም !!

ጋሹ እንዴት እንደተሰደደ? ከበውቀቱ ስዮም

(በ.ስ)

የዚች ጨዋታ መነሻ የሆነኝ የዛሬ ምናምን አመት ያነብኩት “ያረብ ሌሊቶች ” ተረት ነው::

ጋሹ ታታሪና አይናፋር ባላገር ነው:: ሲኖር ሲኖር; በስንት መከራ አንዲት ቆንጆ አጭቶ አገባ::

የሰርጉ ቀን ተበልቶ ተጠጥቶ ጭፈራው ደራ:: ሚዜዎችና አጃቢዎች ሙሽሮች እንዲጨፍሩ ጋበዙዋቸው:: ጋሹ ግብዣውን በስንት መግደርደር ተቀብሎ ይሄን እንቅጥቅጥ ያቀልጠው ጀመር:: ሰርገኛው ክብ ሰርቶ የሙሽራውን እስክስታ ባድናቆት ፈዝዞ መመልከት ጀመረ::

እንክሽ እነካ
እንክሽ እነካ
ይህንን ችሎታ- ደብቆት ነው ለካ!
እንክሽ እነካ
አብዮት ካሳነሽ- በጋሹ ተተካ?

ህዝባዊ አድናቆቱ ብዙ አልቆየም:: ድንገት ከሙሽራው ሱሪ ግድም ቀለል ያለ ፍንዳታ ተሰማ:: የፍንዳታው መንስኤ በሙሽራው ሆድ ውስጥ ሲብላላ የቆየው 59 በመቶ ናይትሮጂን -21 በመቶ ሃይድሮጅን -9 በመቶ ካርቦን ዳይወክሳይድ -7 በመቶ ሜታን -የእስክስታውን ጫና መቁዋቁዋም አቅቶት አፈትልኮ መውጣቱ ነው::

ሙሽራው ክው አለ:: የሙሽሪትም ቆሌ ተገፈፈ
ሰርገኛው ሁላ ሳቁን ከጥቂት ሰከንዶች በላይ ማፈን አልቻለም::

በነጋታው: ጋሹ የፈሱን ሌጋሲ መሸከም ስላልቻለ ሙሽሪቱን ትቶ ከቀየው ተሰደደ:: አምስት አመት ሱዳን በስደት ማቀቀ::

ጊዜው እየጨመረ ሲሄድ ያገሩን ናፍቆት አሸነፈው:: እናም ለመመለስ ቆረጠ::

ድንበሩን ተሻግሮ ያገሩን ምድር ሲረግጥ እንዲት ሴትዮ የበቆሎ ጥብስ ስትሸጥ አገኛት:: ከሴትዮዋ አጠገብ ትንሽ ልጅ ቁጭ ብላ ጠጠር ትጫወታለች::

ጋሹ በቆሎ ገዝቶ ዝምብሎ እንዳይሄድ
“ይቺ ልጅ ስንት አመት ሆናት?” ብሎ ጠየቀ::
ሴትዮይቱ ትንሽ አሰቡና መለሱ-
” አመተምረቱ ትዝ አይለኝም! ብቻ ! ብቻ ሙሽራው ጋሹ በሰርጉ ቀን በፈሳ በሳምንቱ እንደተወለደች ትዝ ይለኛል”

ጋሹ እንደገና ተሰደደ::

እና እኔ እምላችሁ!

የድሜልክ ገድላችሁን -ባንድ ጀንበር ከሚረሳ
ያንዲት ቅፅበት ነውራችሁን -ለዘላለም ከሚያወሳ

ይሰውራችሁ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *