ቴዎድሮስ ካሳሁን ገርማሞ 1. የዛኔው ብላቴናው ቴዲ

ቴዎድሮስ ካሳሁን ገርማሞ
1. የዛኔው ብላቴናው ቴዲ

1994 ዓ.ም፡፡ ያው እንደተለመደው ያም ዓመት ለኢትዮጵያ ርሃብ ነበር፡፡ ስድስት ኪሎ፤ ፋኩሊቲ ኦፍ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ውስጥ ጥቂት “ ትምህርት የማንወድ ” የመረቅንን ልጆች አነሳሽነት ለተራቡ ወገኖች ለመድረስ ያቋቋምነው (ብዙ ታሪክ አለው..) አንድ ቡድንን እመራ ነበር፡፡ ያ እንቅስቃሴ ኋላ ወስዶ ወስዶ ̎ አንድ ብር ለአንድ ወገን ̎ የሚባል እንቅስቃሴን ከሚመሩ ቱባ ቱባ ሰዎች ጋር አገናኘኝ፡፡ ̎ አንድ ብር ላንድ ወገን ̎ ን ከ ̎ ከባድ ሚዛን ̎ ሴት ኢትዮጵያውን መካከል አንዷ ወ/ሪት ሰሎሜ ታደሰ ነበረች የምትመራው፡፡ በየጊዜው እንገናኝ ነበር ልበል እንዴ??!!!
አንድ ብር ላንድ ወገን ዝግጅቱን የሚያጠናቀቀው ሸራተን አዲስ በሚደረግ ቴሌቶንና በመስቀል አደባባይ የሙዚቃ ዝግጅት ነበር፡፡ ሰሎሜን የመጨረሻ ሰዓቱ ዝግጅት ውክብ አድርጎ ሊያሳብዳት ደርሶ ነበር፡፡ሩጫ ነው፡፡ ሥራ ላይ አለቃዬ በሆነች ብለህ የምትመኛት ዓይነት ሰው ነች፡፡ እጅግ ቅልል ያለች የምትወዳት ዓይነት ሴትም ነች-በተለይ ለአጫሽ ትመች ነበር፡፡ እኔ እንኳን ሲጋራ ላይ ̎ ጤባ ̎ ነኝና -ሶሎሜን አባከንኳት….!!…በላይ በላዩ ነበር!!
ከእለታቱ በአንዱ ቀን የትኛው ዘፋኝ በዝግጅቱ መዝጊያ ላይ መገኘት እንዳለበት ሃሳብ በሚያቀርብ ውይይት ላይ እራሴን አገኘሁት፡፡ ሃሳብ ተጠየቅን-ብዙ እንግሊዘኛ ስለማንደፍር ያው ብዙ አማርኛ ዘፋኝ ያቃሉ ተብለን መሰለኝ……ሃሃ!!! ለሸራተኑ ዝግጅት የእኛ የተማሪዎቹ አስተያየት አልተጠየቀም፡፡ ሶሎሜና ሌሎች ̎ የአራዳ ልጆች ̎ ይሆናሉ ያሉዋቸውን መረጡ-እነጥሌ፤ማህሙድና ሌሎችም፤ ጥቂት አጫዋች ሞንደል ሞንደል ያሉ ሴት አዝማሪዎችን ጨምሮ ታጩ፡፡ ከመሃላችን አንዱ ̎ ቴዲ አፍሮ ̎ሲል፤ ሰሎሜ ቀና ብላም ሳታየው አለፈችው፡፡
ቀጥሎ ለመስቀል አደባባይ ለድሃውና ለሰፊው ህዝብ እነማን ይምጡ ተጠየቀ፡በወቅቱ ፖፑላር የነበሩ፤ የሆነ ያአባቱ ስም ነቅአጥበብ የነበረና ሌሎችም እነአረጋኀኝ ጨምሮ ተጠሩ፡፡ ኋላ ላይ በከሲታ ተማሪነት ስርሃት እየተቅለሰለስኩ
̎ ሰሎሜ፤ ቴዲ አፍሮስ? ̎ አልኳት
ሰሎሜ ̎ የቱ?… ይሄ ሃይለስላሴ ምናምን የሚለው ፤ትንሽ ልጅ? ̎ አለችኝ፡፡ ድሮስ ማን ..ቴዲ ልጅ ነው ብላቴና ምናምን …ብለህ ቀባጥር አለው አልኩኝ በውስጤና
̎ አዎ ̎ አልኩ፡፡
̎ ውይ እኔ ይሄ ድንገት ብቅ ብለው እንደርችት በርተው የሚጠፉ ልጆች አልወድም ̎ አለችኝ፡፡
በዛው በከሲታ የተማሪ ቅልስልስነት ይሁን እሺ አልኩ፡፡ በኋላ ብላቴናው ለመስቀል አደባባይ አንሳ ሳይሆን ሃይለስላሴ ጦስ እንደሆኑባት ገመትን መሰለኝ፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም በኋላ ላይ ህዝቡ ቴዲ ቴዲ በማለቱ ባለቀ ሰሃት ተጠራ መሰለኝ፡፡ እውነት ለመናገር እኔም በወቅቱ ቴዲ አፍሮ ከአቡጊዳ ወጥቶ እንዲህ የትውልዴ ክስተት ይሆናል ብዬ አልጠብቅም ነበር፡፡
2. ትንግርተኛው ቴዲ
ከዛ ወዲህ ነው እንግዲህ የካሳሁን ገርማሞ ልጅ ለጠላትም ለወዳጅም ማንነቱን ማሳየት የጀመረው-፡፡ድንገት በርቶ የሚቃጠል ትንሽዬ አምፖል ሳይሆን፤ የጎሳን አጥር ዘለው፤ቅድሚያ ኢትዮጵያን የሚሉ ብዙ ትውልዶች ሁሉ የሚከተሉት መብራት መሆኑን ያሳየው፡፡
ከዚያ ወዲህ ነው ሙዚቀኛነት የባለስልጣናት አጫዋችነት ሳይሆን የህዝብና የሃገር ቁስል የሚታሽበትና የሚታከምበት መድሃኒት ሊሆን እንደሚችል በገሃድ አሳይቶ ፤ማንነቱን ጠላቶቹም ወዳጆቹም ሽቅብ የሚመለከቱበት ማማ ላይ ያስቀመጠው፡፡
ወደድንም ጠላን የዚህች ሀገር ትንሳኤ ላይ ከፍ አርገን ከምንዘክራቸው እልፍ አእላፍ ጀግኖች መሃል ቴዲአፍሮ አንዱ ነው፡፡

3. . ኢትዮጵያ የማለት ዋጋው
ይችን ሀገር በጦርነት ብቻ ሳይሆን በጥበብ ህይወታቸውን የከፈሉላት ብዙ ናቸው፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ ከነዚህ አንዱ ነው፡፡ ሎሬታችን ኢትዮጵያንና ታሪኳን የታሪኳ አካል የሆኑ ነገስታቶችን ሳይታክት ሲዋኝበት ከነበረው የቋንቋ ባህሩ እይቀዳ ዘክሯቸዋል፡፡
ሎሬት ጸጋዬ በትዎድሮስ ቴኣትሩ የአጼ ቴዎድሮስን ምጥ በመድረክ አሳይቶታል፡፡
ተስፋ ባጣ፤ ምድረ በዳ
የአንድ እውነት ፤ይሆናል ባዳ
እናም ትንፋሼ አልሆነሽም፤ሆኜብሽ መራር መካሪ
ሩቅ አሳቢ ፤ቅርብ አዳሪ
ይልቅ መርዶ ላርዳሽ፤ስሚው እኔ እንደሰማሁት
እርም በልተሸ ከምትቀሪ፤ስሚ፤ ገብርዬንም እኮ ጣሉት

እያስባለ ኢትዮጵያንም የቴአትሩን ተመልካችንም አስነብቷል፡፡
ሎሬት ምኒሊክንም ዘክሯል፡፡ሎሬቱ የምኒልክን ጀግንነትና ትእግስት፤ በአባቱ ሳይሆን በኣሳዳጊው በቴዎድሮሰ ከማለ ለምንም እንደማይመለስ በምነሊክ ቴአትሩ ሲያሳይ
ምኒሊክ ሚስጥር የለኝም፤የአንድ እናት ወገን ለወገን
የኛ መድሃኒት፤ እኛ ነን
ኢትዮጵያ ማለት ሰላም ናት፤ለጦርነት አንቸኩልም
ገፍቶ የመጣን ጠላት ግን፤ቴዎድሮስ ይሙት አልምርም
ለዓለም መቀጣጫ እስኪሆን፤ሳልሰብረው አልመለስም

እያለ ሲያስገረመን ኖሯል፡፡
በ80ዎቹ አጋማሽ፤ በዚኁ የብሄር ብሄረሰባታት ዘመን፤ ሎሬቱንና የሎሬቱን ̎ ሃሁ ወይም ፐፑ ̎ ቴኣትር ይዘው በየክፍለሃገሩ ሲዞሩ የነበሩ ወጣቶች መድረክ ላይ ሆነው የክላሽ ቃታ ተስቦባቸዋል፡፡ ይህን ደሞ የሎሬቱ ደቀመዝሙር ከነበሩት ማሃል አንዱ ውኢበስላሴ ግርማ በመድረክ ሲናገር ሰምቼዋለሁ፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ዛሬ የራሱ የእህት ወንድም ልጆች የነበሩ ፤ውሪ የጎሳ ፖለቲከኞች የሚያዋድቋትን ሀገር በጥበብ ምትሃት አንሰቶ ሊያቆማት ከጥቂቶች ጋር ሲነገዳገድ ነው የኖረውና የሞተው፡፡ ኢትዮጵያን ስላለ ብዙ ከፈለ…..ይሄ ትውልድም እንዳልባሌ እንዲረሳው ተደረገ፡፡

ዛሬ ዳግማዊ ጸጋዬን በሌላ ጥበብ የሚያሳየን ቴዎድሮስ ካሳሁን ገርማሞ ብቻ ነው፡፡ እንደጸጋዬ ኢትዮጵያዬ እያለ እየጮኀ ነው ፡፡ ልክ እንደጸጋዬ ለአገር ብዙ የከፈሉ ጀግኖቻችን ያከብራል ይዘክራል፡፡ የሃይሌገብረ ስላሴን የረጅም ርቀት ሩጫን ፍጻሜና የትውልድ ቅብብሎሽን ሥነስርዓት፤ በውብ ሙዚቃ ሸፍኖ ታሪካዊ እድርጎ ቆልፎ አስቀምጦታል፡፡
ብሄር አደለም፤ ሃይማኖት እንኳን የአብሮ መኖራችንና መፋቀራችን ደንቃራ እንደማይሆን አሳይቶናል፡፡ አዛንና ቅዳሴ የሁላችንንም ልብ የሚያሸብር ዜማ እንደሆነ፤ራጉኤል ውስጥ ነጭ ነጠላ ጸጉሯ ላይ የጣለች ባለጨዋ ቀሚሷ ቆንጅዬና አንዋር መስኪድ ውስጥ አምስት ወቅት ሰላቱን የማያዛንፈው ጉብል የልብ ፍቅራቸው ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊ መሆኑን አሳይቶናል፡፡
በዝሆኖች ፀብ ከተሰበረ ድልድይ ማዶና ማዶ ያሉ ቤተሰቦችን ናፍቆት አንጎራጉሮ ሚሊዮኖችን ጣፋጭ እንባ አስነብቷል፤የነገው የቀይ ባህር ወጀብ ጋብ ይልና ትገናኛለችሁ ብሎ ተስፋ ሰጥቷል፡፡
የቴዎድሮስን ምጥና ጭንቀት፤የምኒሊክን ብልሃትና ጀግንነት፤የዚችን መከረኛ አገር የትናሣኤ ተስፋ ሊያሳይ እሞከረ ያለ ከቴዎድሮስ ካሳሁን ውጪ ማንም የለም፡፡ ዛሬ ቴዲ አፍሮ የኮሶና ጨው ችርቻሪዋን የአትጠገብን ብቸኛ ልጅ ካሳን አንስቶ በጎነደርኛ አስለቅሶናል፡፡ ካሳ ብቸኛ ነበር፤ይሄ ነው የሚባል ወነድም ሆነ እህት ባጠገቡ ያልነበረው፤ትልቅ ህልሙን ሊያዋየው የሚችለው የቅርብ ሰው ያልነበረው ̎ ወፈፌ ̎፡፡ የሚያረገው ጠፍቶት ላይታች ሲል ሲዋከብ ያየ ልጁ አለማየሁ እንኳን ̎ አባዬ እብድ ነህ እንዴ ? እብድ ነው ይሉሃል እኮ ̎ ብሎ በጥያቄ የሚያስነባው፡፡ ቴዎድሮስ ደፋር ነው፡፡ በሌላው የጥቁር አለም እጅን ከትከሻ ቆርጠው በቆረጡት እጅ ሲጋረፉ የነበሩ አውሬ ነጮችን ሰንሰለት በእግራቸው አጥልቆ ሲያጓትት የሚውል ልበሙሉ ሰው፡፡ በመጨረሻ ግን ግራ ገባው፡፡ ተደናገረ፤ተዋከበ፡፡ ቴዲ አፍሮ ይህንን በሙዚቃው ሳለለን…ይባረክ!!
ዛሬ ኢትዮጵያ ማለቱ የሚያስጓራቸው ብዙ ናቸው፡፡ ልጅነት የሚባል ያልነበረው የሚመስል ጅብ ካድሬ ቴዲ ድሮ ለምን ይናፍቀዋል እያለ ያለዝንበታል፡፡ ኡኡታ ያስፈልጋል፤የጅብ መንጋ ወሮናል ማለቱ ነው የቴዲ ጥፋቱ፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ከፍሏል-ቴዲ፡፡

4. የዛሬው ብላቴና ቴዲ
ዛሬ ቴዲ ተርታ ዘፋኝ አደለም ፡፡ያ ብልጭ ብሎ የሚጠፋው የተባለው ትንሽ ልጅ አደለም፡፡ ፖለቲካ ነው፡፡ መስከረም 2006 መሰለኝ ባደግ የዩንቨረሲቲ ተማሪዎችን ሰብስቦ ውሎ አበል ይከፍል ነበር፡፡ እግረመንግዱንም የቴዲን አልበም በቀኝ የቀመርን በግራ አስቀምጦ እኔን እዩኝ መሃል ላይ ነኝ ይል እንደነበረ በወቅቱ የአበል ተሳታፊ የነበሩ ልጆች ነግረውኛል፡፡ ዛሬ ቴዲ ብስልና የሚናገረውን የሚያውቅ፤ ንግግሩን ወደልማታዊነት መቀየር እንኳን ኢቲቪ አቅቷት ቤቱ ድረስ ሄዳ የቀዳቸውን ቃለምልልስ ሰርዤያለሁ የሚያስብል ትንታግ ነው፡፡
እባክህ ሚሊየኖችን እንክፈልህ ሸራተን ላይ እኛ የመረጥንልህን ዝፈን ቢሉት ̎ አንገት ከሚሰበር ባይበላስ ̎ ቢቀር ብሎ ከድሆች ጋር በስታዲየም ጨፍሮ፤ከጅማ ልጆች ጋር አቧራ ላይ ተንከባሎ፤ ገነዘብን በሚያመልኩት ሰዎች ፊት መናኛ አድርጎ፤ ዘመኑ የማያውቀውን የክብር ጥግ የሚያሳይ ኩሩ ነው፡፡
በጣም ሊያስመልሰኝ ከደረሱ ነገሮች አንዱ ምንድነው በሉኝ- ምኒሊክንም ሆነ ቴዲ አፍሮን ታመልካላችሁ የሚል የእንዥጥ ካድሬ ብልግና፡፡ ሰዉ እንኳን ሰውን እግዜሩን ማምለክ ካቆመ ሰነበተ፡፡ የባህታዊ ገብረመስቀል ባልንጀራ የነበሩ መናኝ ጳጳሱን እስጢፋኖስ ላይ አንካሴ ወርውረው ሲስቱት፤ ምእመናኑ ̎ እውነትም እግዜር የለም ̎ ብሎ ማምለክ ከተው ከረመ!!
ስማ ስማ፤ስማ… የያዝነው ማምለክ አደለም……ከሱ ትንሽ አነስ ያለ አድናቆት ነው ጌታዬ፡፡ የያዝነው ግርምት ነው፡፡ ከትንሽነት ሣይሆን ከትልቁ ታሪካችን የምትንደረደረው ኢትዮጵያ የበለጠ ግርማ ሞገስ ይኖራታል የሚል ተስፋን ብላቴናችን ባለቀ ሰዓትም ቢሆን ስላቀበለን ነው፡፡
ሆላን ይዘን ጉዞ!!!!
ከtamru huliso

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *