በአጋዚ ጥይት ለመሞትም ጀግንነት ይጠይቃል ፥ እንዲህ ብሎ ያለ ፍርሃት ለመጣፍም ጀግንነት ይጠይቃል !!

በአጋዚ ጥይት ለመሞትም ጀግንነት ይጠይቃል ፥ እንዲህ ብሎ ያለ ፍርሃት ለመጣፍም ጀግንነት ይጠይቃል ! ጀግና ህዝብ ፥ ጀግና ዘር ፥ እልፍ ቆራጥ ይወልዳል ! አሟሟቱን አንዳች ሳይፈራ ይዘክራል ! ይህ የሃውልት ላይ ጥሁፍ ሳይሆን ለቋሚ ጠቋሚ ፥ ለሟች ነብስ ምስክር ምሰሶ ፥ ዋልታ እና ማገር ነው ! በዚህ ሃውልት ላይ የማነበው እና ሃውልቱን ሳየው የማነባው ፥ ሰው ስለሆንኩ ብቻ ሳይሆን ፥ ሰው ስለተቀማሁ ነው ! ያለጊዜው !
ትግሉ ይቀጥላልም ይቀጣጠላልም ! ምልክታችንን ፥ በድንጋይ ላይ ፥ በበራፋችሁ ደጅ ላይ ፥ በትካሻችን ጠባሳ ላይ ፥ በተነቀለው ጥፍራችን ፥ በተሰበረው አፍንጫችን ፥ በኪንታሮት በተሰቃየው አካላችን ፥ እስር ቤት በጠጣነው ውሃ መሰረት በኩላሊታችን በያዝነው ጠጠር ፥ በተፈነከተው ጭንቅላታችን ፥ በድብደባ መካን በሆነው ብልታችን ፥ ወፌ ላላ ስትገርፉን ዘቅዝቃችሁ ረስታችሁ ባጣመማችሁት አፋችን ፥ ባንሸዋረራችሁት አይናችን ፥ ባንክ ሊዘርፉ ነው ብላችሁ በገደላችሁት የስድስት አመት ወንድማችን ፥ የሚቀልጥ ጎማ በእጁ እንዲይዝ ጥይት አቀባብላችሁ ራሱን ሲስስት ትታችሁት በሄዳችሁት ወጣት ፥ በኔ ፥ በሱ እና በእርሷ ፥ በእሳቸው ፥ በነዙ እና በነዚያ ደም ውስጥ ሁሉ ፥ ሲቻለን በሃውልት መልክ ፥ ሲቻለን በእልህ መልክ ፥ ሲቻለን መከራን በቆራጥነት በሚቀበለው ፥ እስርን እና እንግልትና በማይፈራው ደቂቀ ነፃነት ፥ ልቦና እሳት ማንነታችን ይዘን እንዞራለን ! ነፃ እስትንወጣ ፥ እስትናሸንፍ ትንፋሻችን ቢቆም እንኳ ፥ አፅማችን ያረፈበት አሟሟታችንን እየመሰከረ ትግላችንን እንቀጥላለን ! አታቆሙንም ! ምክንያቱም እኛ ሊቆሙ ከተፈጠሩት ትውልዶች ተርታ የምንመደብ አይደለንም እና !
ኄኖክ የሺጥላi

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *