ይህ ዜና ለህወሀት ከመርዶ የከፋ ነው።

ህወሀት የክልል ወኪሎቹን ተልዕኮ ሰጥቷቸው አውሮፓ ልኳቸዋል። የኦሮሚያው ለማ መገርሳ፡ የአማራው ገዱ አንዳርጋቸው፡ የደቡቡ ደሴ ዳልኬና የጋምቤላው ጋትሉዋክ ቱት በህወሀት የተጠረዘላቸውን አጀንዳ ሸክፈው አውሮፓን ለመዞር ትላንት ከስዊዘርላንድ ጀምረዋል። እነዚህ አራት ክልሎች የተመረጡበት ምክንያት ግልጽ ነው። የህዝብ አመጽ እንደ ቋያ እሳት የፈጀው ህወሀት በመሳሪያ ሃይል ለጊዜው እንዲዳፈን ያደረገባቸው አከባቢዎች ናቸው። በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የቀመሳት በትር ክፉኛ ያሳመመችው በመሆኑ ዳግም እንዳትመጣበት በሚችለው ሁሉ እየተፈራገጠ ነው። ሀገር ቤቱን በአስቸኳይ አዋጅ ስር በማድረግ፡ በድርቀት የሚሰቃየውን ካዝናውን ለማርጠብ በሚል ገንዘብ ፍለጋ ሎሌዎቹን ወደ ባህርማዶ አሰማርቷል። እነሱ በእርግጥ ‘ዲያስፖራውን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለማወያየት’ የሚል ችክና አሰልቺ የሆነ ዓላማ አሰቀምጠውለታል።
ህወሀት የውጭ ምንዛሪው እጥረት በአፍጢሙ ሊደፋው ተቃርቧል። ከአሜሪካ በየዓመቱ ከሚሰፈርለት ከ200ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ሊቋረጥ መሆኑ ከሰሞኑ ተሰምቷል። ይህ ዜና ለህወሀት ከመርዶ የከፋ ነው። በምዕራባውያን ገንዘብ እስትንፋሱ ለቆመው ህወሀት መጪው ጊዜ ጥሩ አይመስልም።
አህያ ታርዶም፡ ጸጉር ተሽጦም፡ ሴቶቻችንን ወደ አረብ ሀገራት በ’ህጋዊነት’ ሽፋን export በማድረግም፡ ብቻ እንደምንም የውጭ ምንዛሪው ማግኘቱ የህወሀት የህልውና ጉዳይ ሆኗል። በእርግጥ ዲያስፖራው አድሞበታል። ከ1997ቱ ምርጫ ወዲህ ብዙዎቹ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረኮች ከሽፎውበታል። የዲያስፖራው ልብ ሸፍቷል። ገንዘቡን ለህወሀት እድሜ ማሳጠሪያ እንጂ ማስረዘሚያ ሊሰጥ አይችልም። በተለይ ባለፉት 5ዓመታት ይሄን አረጋግጦለታል። ህወሀት ግን ደረቅ ነው። ሀፍረት የሚባል በመዝገበ ቃላት ውስጥ የለውም። እየጠሉት ‘በፍቅር አበዱልኝ’ ብሎ የሚያብድ፡ ድርጅት ነው። አሁንም ዲያስፖራው ከጎኔ ነው ይላል። አሁንም ዶላር ፍለጋ ውቅያኖስ አቋርጦ ያልማል።
እናም እነ ለማ መገርሳና ገዱ አንዳርጋቸው ዶላሩን በሳምሶናይት አጭቀው ይመለሳሉ የሚል ተስፋ በእነ አባይ ጸሀዬ ልብ ውስጥ ተቀብራለች። የኢኮኖሚ አብዮት የሚባል መሬት የማይወርድ፡ በጨበጣ የታቀደ፡ ልብወለድ ቀመስ ኢኮኖሚያዊ ሰነድ አስታቅፏቸው ከሰሞኑ ልኳቸዋል። ሀወሀቶች የዲያስፖራውን ኩርኩም በተደጋጋሚ ስለቀመሷት አሁን የሚልኳችው አሽከሮቻቸውን ነው። ሲጠሯቸው ‘አቤት’ ሲልኳቸው ‘ወዴት?’ በሚሉ ሎሌዎች እድላቸውን ይሞክራሉ። ለዚህም እነለማና ገዱ፡ ዳልኬና ጋትሉዋክ ተመርቀው ተሸኝተዋል።


ህወሀት በወገኖቹ ላይ በሚፈጽመው መጠነ ሰፊ ስቃይ የሚንገበገበው ዲያስፖራው እየጠበቋቸው ነው። እንደተለመደው ጥሪው በሚስጥር ነው። የስርዓቱ ደጋፊዎችና መሬት ወስደው ቤት የጀመሩ ጥቂቶች ተመርጠው ተጠርተዋል። ከስጋት የተነሳ የውይይት መድረኮቹ በግልጽ በሚታወቁ አዳራሾች ሳይሆን በኤምባሲ ጽ/ቤቶችና በአምባሳደሮች መኖሪያ ቤትች እንዲሆኑ ተፈልጓል። በስዊዘርላንድ የሆነውም እንደዚያ ነው። ያም ሆኖ መረጃው የደረሳቸው ኢትዮጵያውያን በጄኒቭ የአምባሰደሩ መኖሪያ ቤት በድብቅ የተጠራውና የእንግዶቹ ስም በሚስጢር የተያዘው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ተቃውሞአቸውን አቅርበዋል። ለአንድ ሰዓት ገደማ ተቋርጦ የነበረው ስብሰባ በኋላ ላይ በፖሊሶች ጣልቃ ገብነት ቀጥሏል።
እነ ለማና ገዱ አውሮፓን ይዞራሉ ተብሏል።
በአዲስ አበባ ቤት የገነባ አንድ ዲያስፖራ ለምን ህወሀት በሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች እንደሚገኝ ሲጠየቅ የመለሰውን በማካፈል አጭር ጹሁፌን ላብቃ። ‘’እኚህ ሰዎች ክፉዎች ናቸው። የሰራሁትን ቤት ባሌስትራና ጎማ ገጥመውለት እያሽከረከሩ መቀሌ ቢወስዱትስ?!!’’

ከመሳይ መኮንን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *