የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም የህወሃትን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ማስተማመኛ ሊሆን አይችልም!!!

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም የህወሃትን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ማስተማመኛ ሊሆን አይችልም!!!
==================

  1. አርበኞች ግንቦት 7 ርእሰ አንቀፅ

የኢትዮጵያ ህዝብ ከ26 አመታት የህወሃት አገዛዝ በኋላ እየጠየቀ ያለው “በገዛ አገሬ እንደ ሁለተኛ ዜጋ መቆጠሬ ይቁም! አያት ቅድመ አያቶቼ በከፈሉት መስዋዕትነት የባዕድ ወረራን መክታ በነጻነት በኖረች አገሬ ለውጭ ባለሃብቶች እትብቴ ከተቀበረበት ቀዬ መፈናቀሌ ይብቃ! በመንግሥት ሚዲያዎች የሚለፈፈው ልማትና ዕድገት ተጠቃሚው ሥልጣንን የሙጥኝ ያላችሁት እናንተ የህወሃት ልጆችና በአገሪቱ ላይ ለምታካሂዱት ዘረፈ ብዙ የሃብት ዘረፋ ትርፍራፊ እየተወረወረላቸው ሽፋን የሆኑዋችሁ ከዚህም ከዚያም የተገኙ ጥቂት ለግል ጥቅም የተጠጉዋችሁ ግለሰቦች እንጂ እኛ አይደለንም ፤ በአለም አቀፍ ብድር ለተሰሩ ሰፋፊ መንገዶችና ከህዝብ በተዘረፈ ገንዘብ ለገነባችኋቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ስንል ባርነትን በጸጋ አንቀበልም! ኢትዮጵያ የሁላችን እንጂ ነፍጥ ያነገቡ የትግራይ ተወላጆች የግል ሃብት አይደለችም” ፤ ወዘተ የሚል ነው።

የህወሃት አገዛዝ ለዚህ ፍትሃዊ የህዝብ ጥያቄ እየሰጠ ያለው ምላሽ ግን “ምን ታመጣለህ? ደርግን የመሰለ ዘመናዊ ጦር ያደራጀ ሃይል በነፍጥ አስወግጄ ሥልጣን የተቆጣጠርኩት አንተን ላነግስህ አይደለም፤ ወደድክም ጠላህ እኔው ነኝ እምገዛህ”! የሚል የእብሪት ተግባር ነው። የህወሃቱ ቁንጮ የነበረው መለስ ዜናዊ “በደም ተዋጅተን ያመጣነውን ሥልጣን የሚመኝ ካለ እኛ በመጣንበት የአመጽ መንገድ ለመምጣት መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት” በማለት እንደተዛባበተብን ምን ጊዜም አንዘነጋውም። ድህረ መለስ ዛሬ ሥልጣንን ከኋላ ሆነው እየዘወሩ ያሉት እነ ሳሞራ ይኑስ ፤ ጌታቸው አሰፋ፤ ስብሃት ነጋ ፤ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ፤ አርከበ ዕቁባይ፤ አባይ ወልዱ፤ አባይ ጸሃይ ወዘተ በፖለቲካ እይታቸው ብቻ ሳይሆን በትዕቢትና በእብሪት ደረጃቸው ከመለስ ዜናዊ የሚለዩ አይደሉም። ታላቋ ኢትዮጵያ ለነርሱ የሥልጣንና የሃብት ዘረፋ ጥገት ላም መሆኗን ባቆመች ሰዓት መጥፋት ይኖርባታል። በእውናቸውም በህልማቸውም ከዚህ የተለየ ራዕያ ያላቸው ስለመሆናቸው ቢያንስ ያለፈው 26 ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ቆይታ አላረጋገጡም። አንድ አገር በደምና በሥጋ ያስተሳሰራቸውን ወንድማማች ህዝቦች በብሄርና በሃይማኖት በመከፋፈል የጠላትነት ግንብ በመካከላቸው ለመገንባት የተሰሠራው እና አሁንም በመሠራት ላይ ያለው የፖለቲካ ሥራ ይህንን እምነታቸውን የሚያጋልጥ ነው።
በተለይ የሁለቱን ታላላቅ ብሄረሰብ አባላት በዘር ለመለያየት የተሄደበት ረጂም ርቀትና የሁለቱን ታላላቅ ሃይማኖቶች ተከታዮች እርስ በርስ በጥርጣሬና በስጋት እንዲተያዩ ማሴር በኢትዮጵያ ምድር የበቀለ ወገን ቀርቶ ለራሱ አገር ሠላም የሚሻ ጎረቤት አጋሪ እንኳ በእውን ሊያስበው የሚችል ተግባር አይደለም።

እጅግ የሚገርመው በእንዲህ አይነት የለየለት ጠላትነት መንፈስ ውስጥም ሆኖ ህዝባዊ ወያኔ ሃሪነት ትግራይ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት 1983 ጀምሮ የሚጠላትንና አገሬ ብሎ ለመጥራት የሚጸየፋትን አገር በጠመንጃ ሃይል እስከመጨረሻው ለመግዛት ያለውን ዕቅድ ለአፍታም ቢሆን ደብቆ አያውቅም። በዚህ ለዘመናት የመግዛት ዕቅዱ ውስጥ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ሃይል በእርጅናና በሞት ሲለይ ተተኪ የሚሆን ትውልድ “የኔ ነው” ከሚለውን የትግራይ ክልል ለማፍራት የአገሪቱን ሃብት በሙሉ በመጠቀም በእውቀትና በገንዘብ ሌሎች የአገሪቱ ተወላጆች ሊደርሱባቸው የማይችል ዜጎችን የመፍጠር ሥራ በትጋት እየተሰራ ነው። በዚህም የተነሳ ይህንን ዕቅድ ለማክሸፍ የሚንቀሳቀስ ሃይል እንዳይኖር ተቃውሞ ያነሳ ማኛውንም የአገሪቱ ዜጋ በሞት ሊቀጣ የሚችል በኢትዮጵያ ግብር ከፋይ ገንዘብ ደመወዝ የሚቆረጥለት አጋዚ የተባለ ጦር ከተቋቋመ ሰንብቶአል።

በድህረ ምርጫ 97 ወቅት የገዛ ወገኑን አደባባይ ላይ በጠራራ ጸሃይ በመጨፍጨፍ አቅሙ እነ መለስ ዜናዊን አንጄት ቅቤ ያራሰው ይህ አጋዚ ጦር ያኔ የሰበቀውን የግድያ ጎራዴ እስከዛሬ ድረስ ወደ አፎቱ አልመለሰም ። ከህዳር ወር 2008 ዓመተ ምህረት ወዲህ በኦሮሚያ ተጀምሮ ወደ አማራ ክልል የተዛመተውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማክሸፍ ግዳጅ የተሰጠው ታማኝነቱንና አለኝታነቱን ላረጋገጠው ለዚሁ አጋዚ ለተባለው ጦር ነው ። ባለፈው አንድ አመት ብቻ አጋዚ በሁለቱ ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በጥይት ደብድቦ ገድሎአል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩትን ደግሞ ወደ ተለያዩ እስር ቤቶች በማጓጓዝ አስሮአል፤ ገርፎአል፤ ለአካልና ለሂሊና ቁስል ዳርጎአቸዋል። በታሪካችን ተሰምቶ በማይታወቅ ጭካኔ ደምቢዶሎ ውስጥ ልጅ ገድሎ እናት የልጇ አስከሬን ላይ ቁጭ ብላ ግዲያውን እንድታወድስ ለማስገደድ ተችሎአል። ሰሞኑን የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል የነበረው ወጣት ሃብታሙ አያለው እስር ቤት ውስጥ የተፈጸመበትን አሳዛኝ ሰቆቃ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ሲናገር ያልሰማ ሰው ትልቅ መረጃ አምልጦታል። “በወያኔ ዘመን ያልደረሰብን ንቀት፤ ውርደትና መከራ ምን አለ እና ነው መረጃ አመለጠ የሚያስብለ” ሊባል ይችል ይሆናል።

ሆኖም ግን ህወሃት ይህን ሁሉ መከራና ስቃይ የሚያፈራርቅብን ፤ ተቃዋሚዎቹ በሆን ዜጎች ላይ በታሪካችን ሰምተን የማናውቀው አይነት ሰቆቃ የሚያደርስብን በባሪያ ፈንጋይ ዘመን ባሮች ከጎቶቻቸው እንዳያመልጡ እኔን አይተህ ተቀጣ በሚሉት አይነት የቅጣት ዘዴ አርፈው እንዲገዙ ለማሸማቀቅ የተጠቀሙትን ዜደ በኛ ላይ በመጠቀም በፍርሃት እጃችንን አጣምረን እንድንገዛ ለማድረግ ነው። ይህ ከቶ ሊሆን አይችልም ። እንኳን የሰው ልጅ መብት አለም አቀፋዊ ጥበቃ ባገኘበት የ21ኛው ክፍል ዘመን እየኖርን ቀርቶ በዚያ በጨለማው ዘመን ለነጻነታቸውና ለክብራቸው ሲሉ ተዋግተው በወቅቱ በአለም ሃያል የነበሩትን የአውሮጳ ቅኝ ገዢዎችን በሽንፈት የሸኙ የነ ቴዎድሮስ፤ ሚኒልክ፤ በላይ ዘለቀ ፤ አብዲሳ አጋ ፤ ሃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴና የእልፍ አዕላፍ ጄግኖች የታሪክ ወራሾች ብቻ ሳንሆን የነርሱ ወኔና ጀግንነት ዛሬም ድረስ በውስጣችን የሚቀጣጠል ነን።

አርበኞች ግንቦት 7 በጥጋብና እብሪት ተወጥሮ ህዝባችንን በማሰቃየት እስከ ወዲያኛው ለመግዛት የሚያስበውን የህወሃት አገዛዝ ለማስወገድና በምትኩ ፍትህ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈነበት ሥርዓት ለማስፈን ከህወሃት አገዛዝ ጋር የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ያለ አገራዊ ድርጅት ነው።

ህወሃት በመላው አገራችን ውስጥ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማክሸፍ ያስችለኛል ብሎ ያመነበትንና አገሪቱን ሙሉ በሙሉ ወታደራዊ አገዛዝ ሥር ያስገባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ካለፈው ጥቅምት ወር 2009 ጀምሮ በርካታ ግድያዎችን እየፈጸመ ያለው ለነጻነታቸው ሲሉ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ በሽብርተኝነትና በጸረ ሠላም ሃይል እየፈረጀ መሆኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደ አርበኞች ግንቦት 7 አገራቸውንና ህዝባቸውን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ የተሰለፉትን ሃይሎች ለማዳከም ነው ብሎ ንቅናቄያችን ያምናል። ጉልበት ጉልበትን ፤ ግዲያ በቀልን እንደሚፈጥር ያልተረዳው የህወሃት አመራር 500ሺ ጦር ያለውን አምባገነን ሥርዓት ለመጣል የሄደበትንና የተጓዘበትን በማወደስ ከሚጠመድ የመሳሪያ ብዛትና የጦር ሠራዊት ጋጋታ በማያግደው የነጻነት ትግል ላለመበላት ወደ ሂሊናው ተመልሶ በሃይል የያዘውን ሥልጣን በክብር ለባለቤቱ ለሰፊው ህዝብ አሳልፎ ለመስጠት ቢያስብ የበለጠ ይጠቀምው ነበር።

ላለፈው 6 ወራት ሰላምና መረጋጋትን ያላመጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንኳን ለ4 ወር ለ4 አመት ቢራዘም የአዋጁ መራዘም ሊያስከትል በሚችለው ጦስ እንደ አረጀ ዛፍ ውስጥ ውስጡን በምስጥ ተበልቶ እንደሚወድቅ አወዳደቁን ያበላሻል እንጂ የሚያድነው አይሆንም። የአፈና መጠናከር የገታው የነጻነት ጉዞ በታሪክ አልተመዘገበምና የወያኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘም በምንም ምክንያት የወያኔን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም እንደማይችል አርበኞች ግንቦት 7 ያስገነዝባል።

ኢትዮጵያ አገራችንን ለመታደግና የተዋረደውን ሰብዓዊ ክብራቸውን ለማስመለስ የሚንቀሳቀሱ ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን የህወሃትን አገዛዝ ፍጻሜ እናፋጥን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *