የድርቅ አደጋ እየተባባሰ በመሆኑ የተረጂዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው ተባለ

የድርቅ አደጋ እየተባባሰ በመሆኑ የተረጂዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው ተባለ
ኢሳት (መጋቢት 20 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ አራት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በመባባስ ላይ መሆኑን ተከትሎ የተረጂዎች ቁጥር ማሻቀቡን የብሄራዊ አደጋ ኮሚሽን ረቡዕ ገለጠ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና መንግስት በቅርቡ ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር 5.6 ሚሊዮን እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።
ይሁንንና የድርቁ አደጋ በመባባስ ላይ በመሆኑ ምክንያት ቁጥሩ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ኮሚሽኑ ድርቁ እያደረሰ ያለውን ጉዳት አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
ደቡብ ኦሞ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ምስራቅ ሃረርጌ፣ ባሌ ቆላማ ወረዳዎችና የሶማሌ ክልል በውርጭ የተጠቁና የዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር የጨመረባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።
ሃላፊው በእነዚህ አካባቢዎች ለምግብ ድጋፍ የተጋለጡ ሰዎች እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ቢያረጋግጡም፣ ትክክለኛ ቁጥር ለብሄራዊ ምክር ቤቱ ከቀረበ በኋላ ለህዝብ ይፋ ይሆናል ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። ከተያዘው ወር መግቢያ ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የዕርዳታ ተቋማት የድርቁ አደጋ ወደ ረሃብ ሊለወጥ ይችላል ሲሉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት በበኩሉ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ከድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ ከተበከለ ግድብ ውሃን የተጠቀሙ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
የተባበሩት መንግስታት የዕርዳታ ማስተባበሪያ መምሪያ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለቀረበው የእርዳታ ጥሪ ወቅታዊ ምላሽ ባለመሰጠቱ ምክንያት ድርቁ እየተባባሰ መምጣቱን ከቀናት በፊት መግለጹ የሚታወስ ነው።
በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብ ኦሞ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ 268 ወረዳዎች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከ100 የሚበልጡት ወረዳዎች በአንደኛ ደረጃ ተፈርጀው ልዩ ክትትል የሚፈልጉ እንደሆነ ያስታወቁ ሲሆን፣ በተለይ በሶማሌ ክልል ያለው ሁኔታ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።
በተያዘው ሳምንት ወርልድ ቪዥን የተሰኘ አለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋም በኢትዮጵያ ሶማሊያ፣ ሶማሊያና ኬንያ ራሷን ነጻ አድርጋ ባወጀችው በሶማሊላንድ ወደ 700ሺ አካባቢ የሚጠጉ ሰዎች በምግብ እጥረት ሳቢያ ሊሞቱ ይችላሉ ሲል አሳስቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመታደግ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *