”ማእበል” ከፋሲል የኔአለም

ማዕበል
የትኛውም ለህዝብ ነጻነት የሚታገል ድርጅት ከውስጥም ከውጪም ማዕበል ያጋጥመዋል። በማዕ በል ሳይመታ ለውጤት የበቃ ድርጅት በታሪክ ያለ አይመስለኝም፤ ማዕበል የአንድ ድርጅት ተፈጥሮአዊ ባህሪው ነው ማለትም ይቻላል። የትኛውም ድርጅት ማዕበል እንዳይነሳ ማድረግ አይችልም፣ ውስጣዊ ማእበል እንዳይነሳ ማድረግ ቢችል እንኳን ውጫዊ ማዕበሉን በፍጹም ማስቀረት አይችልም። ትልቁ ነገር ድርጅቱ ማእበሉን እንዴት በጥበብ ያልፈዋል የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ላይ ነው። ማእበል ለአንድ ድርጅት አወንታዊ ወይም አሉታዊ ነገሮችን ይዞ ይመጣል። አንዳንድ ድርጅቶች የተነሳባቸውን ማእበል በጥበብ ማለፍ ያቅታቸውና ይጠፋሉ ( የማእበል አሉታዊ ጎኑ መሆኑ ነው)፣ ሌሎቹ ደግሞ ማእበሉን ማለፍ ብቻ ሳይሆን ከማእበሉ ትምህርት ወስደውበት ተጠናክረው ይወጣሉ ( የማእበል አወንታዊ ጎኑ ነው)።
ከፖለቲካ ጋር ባይያያዝም አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ሆላንድ በ1950 ዎቹ በማእበል ተመትታ ከ2 ሺ በላይ ዜጎቿ አልቀውባት ነበር። ከዚህ ማእበል ትምህርት በመውሰድ የባህሩን ከፍታ በኮምፒዩተር የምትቆጣጠርበትን ዘዴ ቀየሰች። ባህሩ ሲሞላ ግድቡን በኮምፒዩተር መልዕክት ትከፍትና ውሃው ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲፈስ ታደርገዋለች፣ ባህሩ ሲጎድል ደግሞ ግድቡን ትዘጋዋለች። ከ1950ዎቹ በሁዋላ በውሃ የተከበበችው ሆላንድ ጉዳት አጋጥሟት አያውቅም። ከማእበል መማር ማለት ይህ ነው።
ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት የሚታገሉ ሃይሎች በማዕበል እየተመቱ እንደሆነ ቢሰማኝም፣ መርከባቸው ልምድ ባላው ካፒቴንና ጽኑ በሆኑ ሰራተኞች እየተመራች በመሆኑ፣ ማእበሉን በጥበብ አልፈውት፣ ካሰቡበት ቦታ እንደሚርሱ አምናለሁ። አልፎ አልፎ ማእበሉን በመፍራትና በማእበሉ በመደናገጥ ከመርከቡ እየዘለሉ ሊወርዱ የሚችሉ ተሳፋሪዎች ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች ከመርከቡ የሚዘሉት ማእበል እንደማያጋጥማቸው አስበው ሊሆን ቢችልም፣ ብዙውን ጊዜ ግን ማዕበሉ እነሱንምሲበላቸው እናያለን። ይህም ያለና የሚጠበቅ ነው። እዚህ ላይ ያልተረጋጉ ተሳፋሪዎች ለመውረድ ሲሽቀዳደሙ የመርከቡዋን ሚዛን እንዳያዛቡ ሌሎች የመርከቧ ሰራተኞች የተደናገጡ ተሳፋሪዎችን የማረጋጋት ስራ መስራት አለባቸው። እንውረድ የሚሉ ካሉም በስርዓት እንዲወርዱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ካፒቴኑ ግን ትኩረቱን ሁሉ በመርከቧ መሪ ላይ ማድረግ አለበት። ትኩረቱን በመርከቧ መሪ ላይ ብቻ ያደረገ ደፋር፣ ልበ ሙሉና ልምድ ያለው ካፒቴን ያላት መርከብ በማዕበል አትሰምጥም። ደፋርና ልምድ የሌለው ካፒቴን የሚዘውራት መርከብ ግን በስኒ ማእበል እንኳን ከመስጠም አትድንም።
የመርከቧ አስተናጋጆች በአንድ መርከብ ውስጥ መንገድ ላይ የሚወርዱና እስከ መጨረሻው የሚዘልቁ ሁለት አይነት ታሳፋሪዎች እንዳሉ ሁሌም ልብ ሊሉ ይገባል። መንገድ ላይ የሚወርዱትን ከአገባባቸው መለየት ይቻላልና በዚህ በኩል ትምህርት ውሰዱ።
ልብ በሉ! የማዕበል እድሜ ምንጊዜም አጭር ነው።
FasilYenealem

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *