እስልምና እንደ ደጀን ብቻ ሳይሆን እንደ ቤተሰብ !

እስልምና እንደ ደጀን ብቻ ሳይሆን እንደ ቤተሰብ

ታላቅ እህት አለችኝ ። የማከብራት ! ፍቅር ካላነሳት የማፈቅራት! የናት አባቴ ልጅ ፥ የኔዋ እህት ሙስሊም ነች ብላችሁ ምን ትሉ? እህቴ እኔ የሁለተኛ አመት ተማሪ ሳለሁ ነበር እስልምናን የተቀበለችው ። ባደግንበት ግቢ ውስጥ እኛ ብቻ ክርስቲያኖች ስንሆን የተቀሩት ጎረቤቶቻችን በሙሉ ሙስሊሞች ናቸው ። ሊያውም አብዛኛዎቹ አረቦች። እህቴም ከልጅነቷ ከነሱ ጋር ያላት ቁርኝት ዕኑ ነበር ። ልክ እኔ ከወንዶቹ ጓደኖቼ ጋ ያለኝ ቁርኝት ፅኑ እንደነበረ ሁሉ ።

በልጅነቴ አያቴ የእስላም ስጋ ( እስላም ያረደውን ) መብላት ሃጥያት ነው ትለኝ ስለነበር ለአቅመ አዳም እስትደርስ የእስላም ስጋን እንደፈራሁት ነው ያደግሁት። ከእስላም ጓደኖቼ ጋ መስጊድ ድረስ ገብቶ እስከመስገድ ደርሻለሁ ፥ ከነሱ ጋ ላለመለያየት ስል ። ይህንን ሁሉ አድርጌ ግን አንድም ቀን እስላም ያረደውን ስጋ ወደ አፌ አስጠግቼ አላውቅም ነበር ። ታዲያ ባንድ ወቅት አንዱ አብሮ አደጌ የሙስሊም ልጅ ( ወሊድ ሳላህ ) እኛ ቤት የፋሲካ ለት እኔን ፈልጎ ሲመጣ ምሳ እየበላን ይደርሳል ። እኔን የእስላም ስጋ ሃጥያት ነው ስትለኝ የነበረችው አያቴ ፥ ወሊድን « ና ምሳ ብላ» ትለዋለች ። ወሊድም ያለ አንዳች ማቅማማት « ቢስሚላህ •••» በማለት የፋሲካውን በግ ያለ አንዳች ጭንቀት አብሮን ይበላል ። ደነገጥሁ! አንደኛ አያቴ እኔን አትብላ የምትለኝን ወሊድን ብላ በማለቷ ግራ ገባኝ ። ለምን አልኩ በውስጤ ። እርግጥ አያቴ እንደምትለው የእስላም ስጋ መብላት ሃጡኣት እንዳልሆነ መገመት ጀመርኩ ።

ታዲያ ይህንን የታሪክ አጋጣሚ በውስጤ አምቄ ስኖር ስኖር ፥ ከለታት በአንዱ ቀን ፥ እህቴ እስልምናን መቀበል እንደምትፈልግ ለቤተሰቡ ተናገረች ። የእስላም ስጋ አትብሉ እያለ ያሳደገን ቤተሰብ እንዲህ አይነቱን ነገር ሲሰማ ምን ሊሰማው እንደሚችል እሰቡት ። እኔ እንኳን መስጊድ ሄጄ ጋደኞቼን ላለማጣት ስል አብሬ የምሰግደው ልጅ ፥ እህቴ የምር ሙስሊም መሆን እንደፈለገች ሳውቅ ደነገጥሁ ። እንዴ ምን ማለትሽ ነው አልኳት ኮስተር ብዬ ። እህቴ በተፈጥሮዋ ረጋ ያለች ሰው ነች ። እስልምናን ለምን መቀበል እንደፈለገች አስረዳችኝ ። በህይወቷ ስትኖር ፥ ከጎረቤቶቻችን ( ከሙስሊሞቹ ) የተማረችው ነገር ፍፁም ሰዋዊ እና ፍቅር የተሞላበት ከመሆኑ አንፃር እስልምና በልጅነታችን ሲነግሩን እንደነበረው አውሬ እንዳልሆነም አስረዳችኝ ። የምትለውን በሙሉ ባውቅም ፥ እንደኔ ቅዳሴ ሲሰማ እምባው ለሚመጣ ልጅ ውሳኔዋ አልዋጥልህ አለኝ ።

ከለታት ባንዱ ቀን እህቴ ሙስሊም አገባች ። ወንድም ነኝና እህቴ ቤት ሄድሁ ። እህቴ ሰልማለች ፥ ሂጃብ ጠምጥማለች ፥ ስናወራ ለመልካሙ ነገር ሁሉ « አልሃምድሊላ» ትላለች ፥ እህቴ ከመሆኗ ውጭ ሌላ ሰው መሰለችኝ ። እንዴት አድርገው ቢያሳድጉን ነው ግን እስልምናን እንዲህ እንዳየው ያደረጉኝ አልኩ ፥ ከፊት ለፊት ቁጭ ብላ ኡዱ ስታደርግ የነበረችውን እህቴን እየተመለከትኩኝ ። የመቅሪብ ሶላት ከሰገደች በኋላ እራት እንደደረሰ ነገረችኝ ። ወዲያ በፍጥነት « ምን ሽሮ ነው ?» አልኳት ። ገና ለገና ስጋ ብላ ትለኛለች እምቢ የእስላም ስጋ አልበላም ብላት ደሞ ትቀየመኛለች እያልሁ በማሰብ ። « አዎ ሹሮ ነው ፥ ግን የተሰራው በእስላም ድስት ነው !» አለችኝ እየሳቀች ።

እህቴ ፈላስፋ ነች ። በህይወት አጋጣሚ መንገዳቸውን ሳያገኙ ቀርተው ፥ ከራሳቸው ጋ ሳይተዋወቁ ከሚኖሩት ጥልቅ ሰዎች ውስጥ እመድባታለሁ ።

« አይ ማለቴ !» አልኳት እየተንተባተብኩ ። ከት ብላ ከሳቀች በኋላ « ሄኒ የሰው ስጋ አትብላ ፥ እሱ ነው ሃጥያት እማዬን ተዋት ! የእማዬ ፍቅር የመንግስቱ ሃይለማሪያም አይነት ፍቅር ነው ፥ እንዲህ አይነት ፍቅር ፥ ህፃን ልጁን በጣም ከመውደዱ የተነሳ አቀፍሁ ብሎ አፍኖ ይገላል » አለችኝ ። ቀጥላም <፥ እንደምትመጣ ሳውቅ ሰላጣ እና ሽሮ ሰርቼልሃለሁ » ስትል ባልተነፍሰውም « እፎይ!» አልኩኝ ። ያ ቀን እንዲያ አለፈ። ቀናት ቀናቶች እየወለዱ ፥ ከለታት ባንዱ ቀን ፥ ከአባቴ ጋ ስለ እህቴ መስለም እናወራለን ። አባቴ በወሎ ክፍለ ሃገር የቡና ና ጨው ዋና ስር አስኪያጅ ሆኖ ለብዙ አመታት ሰርቷል ። እስልምናና እና ክርስትናን ወሎ ውስጥ የኖረ ሰው ሊያየው ይችላል ብዬ የማስብበት የራሴ የሆነ ግምት አለኝ ። እናም እባቴ እንዲህ አለ « እሁን ቤቷ ስንሄድ እንደምን አደርሽ ስንላት አልሃምድሊላህ ብላ ልትመልስልን ነው ማለት ነው ? » አለኝ ። « አዎ ታዲያ ምን ችግር አለው? » አልኩት ለእህቴ በመወገን ። አይ እኔ አሷ ቤት አልሄድም አለኝ ። ለምን ስለው። ይሄን በእስላም ድስት ያማሰለችውን ወጥ አምጥታ ብላ ብትለኝስ ። ጆሮዬን ማመን አቃተኝ ፥ ከአባቴ ጋ ተለያይቼ እህቴን እስከማገኛት ጨነቀኝ ። በፍጥነት ለእህቴ ደውዬ እቤት ዛሬ ማታ ከትምህርት እንደወጣሁ እንደምመጣ ነገርኳት ። ምግብም ያለውን ( የተገኘውን ) እንደምበላ ስነግራት ቀልዴን መስሏት ሳቀች ። ለካስ እህቴን የጎዳት መስለሟ አይደለም ፥ እህቴን የጎዳት እስልምና ቆሻሻ ነው ብሎ የሚያምነው ማህበረሰብ ነው ። ይህ ግን እንዴት ይሆናል ። ቤቷ እንደደረስኩ እህቴ ዛሬ ደሞ ፓስታ ሰርታ ነበር የጠበቀችኝ ። እኔ ስጋ አምሮኛል አልኳት ። ምን ማለትህ ነው አለችኝ በመገረም ። እኔ የእስላም ስጋ አምሮኛል ፥ ይገለኝም እንደሆነ ልየው አምጭልኝ አልኳት ! እህቴ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች ። ከዚህ በኋላ ያለው እምብዛም ነው ። ምን ለማለት ነው ስለ እስልምና ስናገር ፥ የምናገረው ሙስሊሞችን ለማስደሰት አይደለም ፥ ቢሆን ኖሮ አላደርገውም ነበር ። የእስላም ስጋ መርዝ አይደለም ፥ መርዙ የእስላም ስጋ መርዝ ነው ብሎ የሚያስበው አእምሯችን ነው ። በአንድነት እና በፍቅር መክበር ከፈለግን ፥ የጎረቤቶቻችንን እውነተኛ እና የልብ ፍቅር ዋጋ እንስጠው ። እንናገር ካለን ብዙ ታሪክ እለን። ስለማይጠቅም ትተነው እንጂ! አንድ ለመሆን ከፈለግን አንድ በሚያደርጉ ነገሮች ላይ የሆን ብሎ ልዩነቶች አንፍጠር! የሚያመሳስለን ከሚያለያየን ነገር ይልቃልና! የግርጌ ማስታወሻ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት ይከብዳል ፥ ለመረዳትም እንዲሁ። እኛ ስጋውን ከመብላት ከሚመጣው ሃጢያት (እንደ እምነታችን ) የበለጠ ፥ በራሳችን ጨቅይተናል ። ከጨቀየንም ቆተናል! የኢስላም ስጋ ብሉ እያልሁ አይደለም። ስለ ፍቅር እና አንድነት ስናወራ፥ በልቦናችን የጠመቅነው ፥ መንገሽገሽ ከውስጣችን ሊወጣ ( ስፍራውን ለፍቅር ለቆ ሊሄድ ይገባል ) ነው ። ያኔ ስጋው ጠላታችን እንዳልሆነ ይገባናል ። አሁን ባለው ሁኔታ ፥ በ ወጥ ቤት እንኳ ሳንግባባ እንዴት ባገር ጉዳይ ለማለት ነው ። ይህ ነገር በእስልምና አማኞች ዘንድ የሚኖረው እንድምታ ተመሳሳይ ነው። በምግብ ባይገለፅ እንኳ አንኳር የሆኑ ተፃራሪ ሃሳቦችን በማፍለቅ አንድነትን የሚንዱ ግን ደሞ ስለ እምነት ሲባል የሚባሉ የሚመስሉ ነገሮች ( ችግሮች ) አሉ ። በግራም በቀኝም! ዋናው ቁም ነገር ሰው እንሁን ነው ! ኄኖክ የሺጥላ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *