የግብጽ ካርድ ተመዟል ከመሳይ መኮንን!

የግብጽ ካርድ ተመዟል

ግብጽ እየተላመጠች ነው። በህወሀቶች እየታኘከች ነው። በህወሀት ዘንድ ከመንደር ካድሬው እስከ ቱባው ባለስልጣን፡ ቴሌቪዥኑና ሬዲዮው፡ ግብጽ ላይ ውጉዝ ከማርዮሱን እያዘነቡት ነው። በኢትዮጵያውያን የተቀጣጥለው የነጻነት ትግል ውስጥ የግብጽ እጅ አለበት የሚል ዜማ በሚገባ እየተቀነቀነ ነው። በአንድ ቂ….* መፍሳት እስኪቀራቸው በፍቅር ሰክረው መሰንበታቸውን ወደጎን አድርገው ነጋ ጠባ ግብጽን መራገም የህወሀት የጊዜው የፕሮፖጋንዳው ማጠንጠኛ አቅጣጫ ሆኗል። የአባዱላ ቃለመጠይቅ እንዴት ይረሳል? ” One said..love never die..if there is a love a trust between us ..never die…ረጅም ሳቅ….” ። ለግብጽ ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንዳልተባለ ዛሬ ‘አይንሽን ለአፈር’ እየተባለ ነው።

ይህ አካሄድ ሁለት መልእክቶችን ያስተላልፋል። አንደኛው የኢትዮጵያን ህዝብ ብሄራዊ ስሜቱ ተኮርኩሮ ”ዘራፍ ሀገሬን አትንኩ” ብሎ ይነሳል። ከጎኔም ይቆማል’ የሚል ተስፋ በህወሀቶች ልብ ውስጥ እንደሚኖር መገመት አይከብድም። ሁለተኛው ‘የኢትዮጵያ ህዝብ መንግስት እንዲለወጥ አይፈልግም። ተስማምቶታል። የሌላ ሃይል ግፊት እንጂ በህዝቡ ዘንድ ያለው ስሜት ሌላ ነው ‘ የተሰኘ ንቀትና ድንቁርና የፈጠረው አካሄድ ነው።

ለግብጽ ከህወሀት በላይ ማንም ቅርብ እንዳልሆነ የማይታወቅ ከመሰላቸው ሞኞች ናቸው። በሻዕቢያ መሪነት፡ በአሜሪካ ረዳትነት፡ በግብጽ አጋፋሪነት 4ኪሎ ቤተመንግስትን መቆጣጠራቸውን የዘነጋን ከመሰላቸው ቂሎች ናቸው። የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፈው በመስጠት ሀገሪቱን ሽባ አድርገው በመላው ዓለም ለብሄራዊ ውርደት እንድንበቃ ማድረጋቸውን ያልተገነዘብነው አድርገው ከወሰዱት ጅሎች ናቸው። የአባይን ወንዝ በተመለከተ በ1993 ዓም ሟቹ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያን ጥቅም አፈር ከድሜ ያበላበትን ስምምነት መፈራረሙን ያላወቅን መስሏቸው ከሆነ በጽኑ ታመዋል ማለት ነው። ብዙ ንገሮችን ማንሳት ይቻላል።

እናም ጨዋታን ነቅተናል። ነቅተንም ጠላትን ለይተናል። ግብጽ ለኢትዮጵያ የምንግዜም ባላንጣ መሆኗን እናውቃለን። ህወሀትን የመሰለ ጸረ ኢትዮጵያ ጨቋኝና ዘረኛ ስርዓት ተሸክመን ስለግብጽ ጠላትነት ማውራት ቅንጦት ነው። ቤታችንን የሚያተራምሰውን ኋላቀርና በድንቁርና የደለቡ የአንድ መንደር ሰዎች የሚመሩትን ገዢ ስርዓት አስቀምጠን ግብጽ ላይ ‘ዘራፍ’ ማለት ጅልነት ነው። ለግብጽ እንደርሳለን። በቅድሚያ ህውሀትን ከነጉድፍ ታሪኩ ማሰናበት ግድ ይላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *