የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገዛዙ ከውድቀት በሁዋላ ! ከፋሲል የኔ አለም

#EthiopiaRevolution የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገዛዙ ከውድቀት በሁዋላ የሚጸጸትበት ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካም በወሳኝ መልኩ የሚቀይር መሆኑን አምናለሁ። ውሳኔው የአገዛዙን መዳከምና መፈራረስ የሚያመለክት በመሆኑ በውስጥ ያሉ የነጻነት ታጋዮች “የሞራል” ብርታት አግኝተው ለመጨረሻው ድል ጥርሳቸውን ነክሰው እንዲታገሉ ያደርጋቸዋል። ከአገዛዙ ጋር ለ25 ዓመታት የተጓዙ የውጭ ሃይሎችም አሮጌውን ስርዓት ወግድ ብለው ከአዲሶቹ ጋር መቀራረብ የሚፈጥሩበት እድል ይፈጥርላቸዋል። የአገሪቱ ዜጎችም ሆኑ የውጭ ሃይሎች የ 6 ወሩን የአዋጅ ጊዜ፣ አገዛዙ ሃብቱን የሚያሸሽበትና የወደፊት ማረፊያውን የሚያመቻችበት ጊዜ አድርገው ይወስዱታል። በኢህአዴጎች መካከል ያለው አለመተማመን ይሰፋል። ወደ ውጭ የሚደረግ የባለስልጣነት ጉዞ በጥርጣሬ ይታያል፤ እርስ በርስ መካሰስና መወነጃጀል ይጨምራል። ነጋዴው ለአሮጌው አገዛዝ ለመገበር ፈቃደኛ አይሆንም፣ ባለሃብቱም ተማምኖ ኢንቨስት ለማድረግ አይደፍርም። የመንግስት ሰራተኛውም “ካደሬውን ምን ታመጣለህ?” እያለ አገዛዙን ለመጣል የራሱን ትግል ይጀምራል። ኢኮኖሚው በእጅጉ ይዳከማል። አበዳሪዎች ገንዘባቸውን መልቀቅ ያቆማሉ። ለፖሊሶች ወታደሮችና ደህንነቱ የሚከፈል በቂ ገንዘብ ይጠፋል። ወታደሩ “ካልተከፈለን አንገድልም” ማለት ብቻ ሳይሆን፣ እስከዛሬ ላገለገልንበት በበቂ አልተከፈለንም በማለት በአመራሩ ላይ እርምጃ መውሰድ ይጀመራል። ብዙ ነገሮችን መዘርዝር ይቻላል። ዞሮ ዞሮ የሚደረስበት ድምዳሜ ግን አንድ ይመስለኛል- አዋጁ የአገዛዙን ፍጻሜ የሚያበስር ደወል መሆኑን።

– Fasil Yenealem

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *