ጀግናው ብ/ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ! የመጨረሻ ስንብት ቀን ተፈፀመ!

የታላቁ ጀግና ስንብት

ብ/ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ከኢትዮጵያ አየር ሃይል የበረራ ጀግኖች መካከል አንዱ ነበሩ። የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ከመቀላቀላቸው በፊት በ1956 ዓም ሃረር አካዳሚ በመግባት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በሃረር አካዳሚ ቆይታቸው ወቅት የጠለቀ የውጊያ ስልት፣ ወታደራዊ አመራር፣ የአካል ብቃትና የወታደራዊ ሳይንስ ስነምግባር በመማር በመኮንንነት ተመርቀዋል።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል ስመጥር በሆነው የሃረር አካዳሚ ምልመላ በሚያካሂድበት ወቅት ብ/ጀኔራል ለገሰ ተፈራ ብቁ ሆነው በመገኘታቸው አየር ሃይልን ተቀላቀሉ። በ1959ዓም ትምህርታቸውን አጠናቀው የበረራ ክንፋቸውን ከገኙ በኋላ የጄር አብራሪና አስተማሪ ሆኑ። ብ/ጄኔራል ለገሰ ተፈራ በየጊዜው በሚያሳዩት የሙያ ብቃት ምክንያት ከሌሎች መካከል ተመርጠው በተዋጊ አውሮፕላን በረራ አስተማሪነት ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል።
ወራሪው የሱማሊያ መንግስት የግዛት ተስፋፊነት ምኞቱን ለማሳካት ኢትዮጵያ በወረራ ጊዜ ብ/ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ጀግንነት ፈጽመዋል። በዚያድባሬ ወረራ ወቅት የዘጠነኛው ስኳድሮ ተዋጊ የነበሩት ብ/ጄኔራል ለገሰ ተፈራ፣ በግላቸው አምስት የሶማሊያ አውሮፕላኖች በአየር ላይ ውጊያ በመምታት ጥለዋል። የቡድን አባሎቻቸው ከሆኑት ኮረኔል ባጫ ሁንዴ፣ ብ/ጄኔራል አሸናፊ ገ/ጻዲቅ፣ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ፣ ሜ/ጄኔራል አምሃ ደስታና ሌሎች የኢትዮጵያ ጀግኖች ጋር በመሆን የሱማሊያን ወራሪ ሃይል ለመደምሰስ በተደረገው ጦርነት አንጸባራቂ ድል አስመዝግበዋል።
ብ/ጄኔራል ለገሰ ተፈራ በወራሪው የሱማሊያ ጦር ላይ ባደረሱት ከፍተኛ ምትና ጉዳት ኢትዮጵያ ለተጎናጸፈችው ድል ላበረከቱት የጀግንነት ስራ የህብረተሰባዊነት ኢትዮጵያ ጀግና የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳሊያ ተሸላሚ ከሆኑት ሶስት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ለመሆን ችለዋል።
ከ11 ዓመት የሱማሊያ እስር ቤት ቆይታ በኋላ ወደ ሃገራቸው በመመለስ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገል ባላቸው ፍላጎት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ አየር ሃይል ተመልሰው የበረራ አስተማሪ በመሆን አገልግለዋል። ሆኖም ባደረባቸው የጤና መታወክና ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ብዙ መቀጠል አልቻሉም። ይባስ ብሎ በግንቦት 83 በተከተሰተ የመንግስት ለውጥ ምክንያት ውጥናቸው ሳይሳካ ቀርቶ ወደ አሜሪካን ተሰደዱ።
የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑት ብ/ጄኔራል ለገሰ ተፈራ፣ ያፌት ለገሰ፣ ነጻነት ለገሰ እና ሉሊት ለገሰ የሚባሉ የሶስት ልጆች አባት ነበሩ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *