ይድረስ ለራጩ ቀነኒሳ ከደረጀ ሀብተወልድ !

እልህና ቅናት ለበጎ ሲሆን ያሳድጋል፤ ለክፋትና ለምቀኝነት ሲውል ግን ይዞን ይጠፋል።ቀነኒሳ በልጅነቱ እልኸኛ እንደነበር ሲወራ ሰምቻለሁ። አንድ የአካባቢው አባት እልከኝነቱን ሲገልጹ ፦”ልጆች ጋር አኩሉሉ ሲጫዎት ሳይቀር እነሱ ጓሮ፣ ጓዳ ሲደበቁ የሱ ተራ ሲደርስ ከበቆጂ- አሰላ ድረስ ሄዶ ነበር የሚደበቀው” ብለዋል ይባላል።እንዳጋጣሚ ይህ እልኩ መልካም ሆኖለት ዛሬ ለደረሰበት የሩጫ ንጉሥነቱ ጠቅሞታል።ታላቅ አትሌት አድርጎታል።
በአንጻሩ በሪዮ ኦሎምፒክ”ብቁ አይደለህም” ተብሎ ሳይመረጥ በመቅረቱ ከአሰልጣኞቹ ጋር እሰጥ እገባ ውስጥ መግባቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ካሳምንት በፊት ደግሞ ፈይሳ ሌሊሳ ፦” እነ ኃይሌና ቀነኒሳ ህዝብ እየተገደለ ባለበት ሰዓት ስለውጤት መጥፋት ከሚብሰከሰኩ እየሞተ ላለው ሕዝብ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ አቀርብላቸዋለሁ።” ብሎ ነበር። ለዚህ የፈይሳ ጥሪ እነሆ የቀነኒሳን ምላሽ አዬነው።ቀነኒሳ በአሁኑ ቃለ-ምልልሱ ያለውን ነገር ለማለት ሀገር ቤት ያለው ሀብቱና ከመንግስት ጋር ያለው ቅርበት ተጽዕኖ አላደረገበትም እያልኩ አይደለም። በዘመዶቹና በቤተሰቦቹ ላይ እየሆነ ያለውን እውነታ በዐይኑ እያዬውና በጆሮው እየሰማው ረዥም ርቀት ሄዶ ፈይሳን ጭምር ለመተቸት የሞከረው ከእልኸኝነት ባህርይው ተነስቶም ጭምር ነው ባይ ነኝ።
ቀነኒሳ ሆይ፣
“ቀነኒሳ አንበሳ”ይባል እንደነበረው ሁሉ “ፈይሳ አንበሳ” መባሉ ግድ ነው። ለፈይሳ የአንበሳነት ክብርን ያጎናጸፍነው የአንተን አንበሳነት ክብር ገፈን አይደለም። ያኔ አንተ አንበሳ ስትባል ፈይሳ እንደዘመረልህ ሁሉ ዛሬ ታናሽ ወንድምህ ለዚህ ክብር ሲበቃ ደስ ሊልህ በተገባ ነበር። ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ አንተ፣ደራርቱ፣ ጥሩነሽ፣ ገንዘቤ፣ ፈጡማ ሮባ፣ መሰረት ደፋር፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ ሚሊዮን፣ምሩጽ፣ በላይነህ ወዘተ…..የሀገራችንን ስም በዓለማቀፍ መድረክ በማስጠራት ታላቅ ጀብዱ መፈጸማችሁን መቼም አንረሳውም። ቢመራችሁም፣ ቢጣፍጣችሁም አንድ እውነት ግን እንነግራችኋለን፦ ጀግናው ፈይሳ ሌሊሳ ደግሞ ከሁላችሁም የበለጠውን እጅግ ታላቁን ገድል ፈጸመ።
ልዩነታችሁም አንተ ሪዮ ባለመሂድህ ለራስህ እንዳለቀስክና – ፈይሳ በሪዮ አሸንፎ ለሕዝቡና ለወገኑ እንዳለቀሰው ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *