በአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ ቀጥሏል፣ ገበሬዎች የአጋዚ ወታደሮች ጋር እየተጋፈጡ ነው ኢሳት ( ነሃሴ 25 ፥ 2008)

በአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ ቀጥሏል፣ ገበሬዎች የአጋዚ ወታደሮች ጋር እየተጋፈጡ ነው
ኢሳት ( ነሃሴ 25 ፥ 2008)
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ እና ምስራቅ ጎጃም የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ ወደሌሎች ዞኖች እየገሰገሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት መደበኛ ጦር በማንቀሳቀስ ተቃውሞን ለማፈን እየሞከረ መሆኑ ተነገረ።
በአማራ ክልል የሚገኘው ህዝብ ተቃውሞውን በቤት ውስጥ አድማ በማድረግ የትግል ስልቱን መቀየሩና ሌሎች አካባቢዎችም እንደሁኔታው የትግል ስልታቸው እየቀያየሩ እንዲታገሉ ጥሪ ቀርቧል።
ከሁለት ሺ በላይ መደበኛ ጦር በአማራ ክልል ያሰማራው ህወሃት የሚመራው መንግስት፣ ህዝባዊ ተቃውሞን ለማዳከምና ብሎም ለማስቆም በወሎ በኩል ብዛት ያለው ጦር ወደ አማራ ክልል በኩል ለማስገባት የሞከረ ሲሆን፣ ይህ ጦር ወደ ጎንደር እና ጎጃም እንዳያልፍ (እንዳይገባ) የጋይንት ህዝብ ድልድዩን በመስበሩ ጨጨሆ አካባቢ ጉዞው ተሰናክሎ እንዲቆም ተደርጓል።
የከተማውና የገጠር ነዋሪው የጋይንት ህዝብ በአንድነት በመተባበር ጦር ሰራዊቱ እንዳያልፍ እየተከላከለ እንደሚገኝ ተገልጿል። በወሎ በኩል ወደ ጎጃምና ጎንደር ጦሩን ለማሰማራት የሞከረው የህወሃት/ኢአዴግ መንግስት፣ በጎጃም በኩል ቀጥታ ህዝቡ አያሳልፈንም በማለት ያሰበ ሲሆን፣ የጋይንት ህዝብ ጨጨሆ ላይ ድልድይ በመስበር ጦሩ ወደ ጎጃም እና ጎንደር እንዳያልፍ ማድረጉን እማኞች ከስፍራው ዘግበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በወገራ ወረዳ አምባጊዮርጊስ ከተማ ትናንትና ዛሬ በገበሬዎች እና በመንግስት ሃይሎች መካከል በተከሰተው ግጭት ከታጣቂዎችም ከአርሶአደሮችም ጉዳት መድረሱ ታውቋል። በግጭቱ ከገበሬዎች 8 ከመንግስት ታጣቂዎች ደግሞ 12 ሰዎች መቁሰላቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ የመለክታል።
በመተማ ህዝባዊ እምቢተኝነት ተቀስቅሶ የመንግስት ሰላይ የሆኑ ሰዎች ንብረት መቃጠሉ ታውቋል። በሸኽዲም እንዲሁ ከፍተኛ ህዝባዊ እምቢተኝነት መቀስቀሱ ተሰምቷል።
በተመሳሳይም፣ በደባርቅ ከተማ በመንግስት ሃይሎችና በህዝቡ መካከል በተነሳው ግጭት 1 ሰው መገደሉንና 6 ሰዎች መቁሰላቸውን እማኞች ከስፍራው ለኢሳት ገልጸዋል። ከጎንደር ወደ ትግራይ ዱቄትና ዘይት ጭኖ ይጓዝ የነበረ ተሳቢ መኪና በደባርቅ ከተማ እንደተቃጠለ ለማወቅ ተችሏል።
በጎንደር ከተማ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ባለመረጋጋት ወስጥ የነበሩት 21ሺ የሚሆኑ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ግቢውን ለቀው በመውጣት ወደ አካባቢያቸው እየሄዱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
የአማራ ክልል መዲና የሆነችው ባህርዳር ከተማ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ ቀበሌ 14 በሚባለው አካባቢ በመንግስት ታጣቂዎችና በገበሬዎች መካከል ከፍተኛ ተኩስ እንደሚሰማ እማኞች ከስፍራው ዘግበዋል። ሌሎች የባህርዳር ከተማ ክፍል በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ከዚህ በፊት ለአበባ እርሻ መሬታቸውን በግዳጅ የተነጠቁ በባህርዳር ዙሪያ የሚገኙ ገበሬዎች በርካታ የእርሻ መሳሪያዎችን ማቃጠላቸው ተሰምቷል። ሁለት የህንድ የአበባ እርሻዎችም መቃጠላቸው ተሰምቷል።
በህወሃት አጋዚ ጦር በታጠረችው በደብረማርቆስ ከተማ የቤት ውስጥ አድማ በተጠናከረ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት በከተማዋ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደማይታይ እማኞች ለኢሳት ከስፍራው ተናግረዋል። የቤት መቀመጥ አድማ ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት እንደሚደረግ ከአሰባባሪዎቹ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ብዛት ባላቸው የጎጃምና የጎንደር ከተሞች ህዝቡ የህወሃት/ኢህአዴግን አስተዳደር በማስወገድ የጎበዝ አለቆች እየሾመ እየተዳደረ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል። በርካታ የብዓዴን አባላት ከህዝቡ ጎን በመሰልፍ ለትግሉ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረጉ እንደሚገኙ ከተለያዩ የአማራ ክልሎች የደረሰን ሪፖርት ያስረዳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *