አንድ የቀድሞ ከፍተኛ የአጋዚ ክ/ጦር አዛዥ፣ ጦሩ አፈሙዙን ወደ አዛዦቹ እንዲያዞር ጠየቁ

አንድ የቀድሞ ከፍተኛ የአጋዚ ክ/ጦር አዛዥ፣ ጦሩ አፈሙዙን ወደ አዛዦቹ እንዲያዞር ጠየቁ

ኢሳት (ነሃሴ 24 ፥ 2008)
በአማራና በኦሮሚያ ክልል በተቀጣጠለው ህዝባዊ እምቢተኝነት በመንግስት የግድያ ትዕዛዝ የተሰጠው የአጋዚ ጦር ወደ ህዝቡ እንዳይተኩስ እና መሳሪያውን ወደ አዛዦቹ እንዲያዞር አንድ የቀድሞ ከፍተኛ የአጋዚ ክ/ጦር አዛዥ ጠየቁ።
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተነሳውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ መንግስት ያሰማራቸው የጸጥታ ሃይሎች ህዝቡን በመግደል ላይ መሆናቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳዘናቸው ለኢሳት የገለጹት የቀድሞ አጋዚ ክ/ጦር መስራችና አመራር ኮሎኔል አለበል አማረ፣ የክ/ጦሩ አባላት ከህዝቡ ጋር በመወገን ታሪክ የመስሪያው ጊዜ አሁን መሆኑን ተናግረዋል።
የአጋዚ ክ/ጦር መስራች የሆኑት ኮሎኔል አለበል አማራ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ወደ ኋላ በመሄድ በምርጫ 97 የተፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን አስታውሰዋል። በምርጫ 97 በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ህዝቡን ለመጨፍጨፍ በአሮጌው አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ ዋና የማዘዣ ጣቢያ ተቋቁሞ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህን የማዘዣ ጣቢያ የሚመሩት ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች እና 12 የህወሃት አባል የሆኑ ጄኔራሎች እንደነበሩ አስታውቀዋል።
ማዘዣ ጣቢያውን የመሩት የፖለቲካ አማራሮች አቶ መለስ ዜናዊ፣ አቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ እና አቶ ሙሉጌታ አለምሰገድ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ከፖለቲካ መሪዎች ትዕዛዝ እየተቀበሉ ግድያውን ሲያስፈጽሙ የነበሩት 12 ጄኔራሎች በስም ዝርዝር የገለጹት ኮሎኔል አለበል አማረ፣ ሁሉም ጄኔራሎች የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው በሰራዊቱ ውስጥ ጥያቄ አስነስቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
የቀድሞ የአጋዚ ክ/ጦር ከፍተኛ መሪ የነበሩት ኮሎኔል አለበል አማረ፣ አሁን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ለመቀልበስ ተመሳሳይ የሆኑ አደረጃጀቶችና ማዘዣ ጣቢያዎች እንዲሚቋቋሙ የገለጹ ሲሆን፣ ምስኪኑ ተራ ወታደር ወደህዝቡ መተኮሱን አቁሞ በቅምጥል ህይወታቸውን እየመሩ ወዳሉት አዛዦች አፈሙዙን ማዞር ይኖርበታል በማለት ተጽዕኖአቸውን አቅርበዋል።
ተራው የአጋዚ ወታደር እንደሌላው ኢትዮጵያው በድህነት ውስጥ የሚኖር፣ ከህዝቡ አብራክ የወጣ እና በህዝቡ ውስጥ የሚኖር በመሆኑ እየተካሄደ ያለውን የህዝብ ቁጣ ይገነዘባል ያሉት ኮሎኔል አለበል፣ ሰራዊቱ በህዝቡ ድጋፍ ከተደረገለት አፈሙዝ በዘረኝነትና የቅንጦት ህይወት ወደ ሰከሩት የጦር አዛዦች እንደሚያዞር ጥርጥር እንደሌላቸው አስታውቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *