ህወሃት/ኢህአዴግ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞን በሃይል ለመጨፍልቅ ከሞክር ውጭ አማራጭ እንደሌለው ተገለጸ

ህወሃት/ኢህአዴግ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞን በሃይል ለመጨፍልቅ ከሞክር ውጭ አማራጭ እንደሌለው ተገለጸ
ኢሳት (ነሃሴ 18 ፥ 2008)
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ እምቢተኝነት በከፍተኛ ሁኔታ አድማሱን እያሰፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ የኢህአዴግ መሪዎች በስልጣን ለመቀጠል ዋስትና ስለማይኖራቸው በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚወስዱትን የሃይል እርምጃ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንድ አለም አቀፍ ተቋም ገለጸ።
Foreign Policy Group ተብሎ የሚጠራውና የአለማችንን ጉዳዮች የሚተነትነው ቡድን የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የኢህአዴግ መሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የጠበበውን የፖለቲካ ምህዳር ከማስፋት ይልቅ ለህዝቡ ስራ በመፍጠር፣ ሙስናን በማስቀረት፣ እና የማህበራዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት የተጀመረውን ተቃውሞ ለማርገብ እንደሚረባረቡ ባወጣው ጽሁፍ ገልጿል።
የጸረ-ህወሃት አቋም በከፍተኛ ሁኔታ በጋለበት በአሁኑ ወቅት፣ የአገሪቷን 34% የሚሆኑ የኦሮሞና 27% የሚሆኑ የአማራ ብሄረሰብ አባላት የዘር መድሎ ተፈጸመብን ብለው እንደሚያስቡና አሁን በስልጣን ላይ ያለው አምባገነናዊ ስርዓት አንገፍግፏቸው እንደሚገኝ ፎሪን ፖሊሲ ትናንት ባወጣው ትንታኔ አስረድቷል። በአሁኑ የመንግስት አወቃቀር የኦህዴድና የብዓዴን ባለስልጣናት በመንግስት አስተዳደር ስርዓት ከህወሃት በተቃረነ መልኩ ምንም አይነት ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም እንደሌላቸው ገልጿል።
የተለያዩ አለም አቀፍ የማህበረሰብ አባላት ባለፉት 25 አመታት ህወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲያሰፋ የመንግስት አወቃቀር ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ቢመክሩም፣ ህወሃት/ኢህአዴግ በተቃራኒው ዜጎችን በማሰር፣ በመግደል፣ እንዲሁም ከአገር በማባረር እና ጨቋኝ ህጎችን በማውጣት ዜጎችን ዝም ለማሰኘት ሞክሯል ሲል Foreign Policy Group በጽሁፉ አብራርቷል።
በአሁኑ ሰዓት በአማራና በኦሮሞ ማህበረሰቦች ላይ የዘር መድሎ እና መገለል ተባብሶ በመቀጠሉ፣ በእነዚህ ክልሎች ጸረ-ህወሃት ስሜቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተንጸባረቁ እንደሚገኙ ይኸው Foreign Policy Group በሃተታው አስፍሯል።
በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተነሱትን ህዝባዊ ተቃውሞዎችን የዳሰሰው ይኸው ሪፖርት፣ በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች የተነሳው ተቃውሞ የወልቃይት ጉዳይን ተንተርሶ እንደሆነ ገልጾ፣ ወልቃይትን በትግራይ ክልል መካለሉ ለሁለቱ ህዝቦች የተቀበረ “ፈንጅ” እንደሆነ ተገልጿል። የአማራ ክልል ሰላማዊ ሰልፈኞች የህወሃት ባለስልጣናት የፌዴራል መንግስቱን ከለላ በማድረግ ወልቃይትን ወደ ትግራይ አካለዋል ብለው እንደሚያስቡም ፎሪን ፖሊሲ በሪፖርቱ አትቷል።
በኦሮምያ ክልል የተነሳው ተቃውሞ የራስ አገዛዝን በማስፋት ላይ የተመሰረተ ነው ያለው የፎሪን ፖሊሲ፣ ክልሉን የሚያስተዳድረው ኦህዴድ በሙሰኞች የተሞላ አባላቱም የህወሃት አገልጋዮች ናቸው ብሏል።
ከወራት በፊት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ቀጣይ እንደሆነ የዘረዘረው Foreign Policy Group፣ በአማራና ኦሮሞ ህዝብ መካከል የአንድነትና የመደጋጋፍ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደመጣና በውጭ የሚገኙ ሁለት ፓርቲዎች አንድነት በመፍጠራቸው የትግሉን አቅጣጫ ከፍ አደርገዋል ብሏል።
ህወሃት/ኢህአዴግ ለአስርተ አመታት ስልጣን ያለገደብ እንደነበረው የሚገልጸው ፎሪን ፖሊሲ፣ የህወሃት/ኢህአዴግ መሪዎች ህዝባዊ ተቃውሞን ለማርገብ አቅም እንደሌላቸው፣ ለራሳቸው ህልውናም ፈታኝ እንደሆነባቸው አስረድቷል
የህወሃት/ኢህአዴግ መሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን ቢከፍቱ ለራሳቸው ህልውና ስለሚያሰጋቸው፣ ህዝባዊ ተቃውሞውን በሃይል ለመፍታት እንደሚጥሩ ፎሪን ፖሊሲ አክሎ ገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *