ጨዋታ ከፈጣኑ ኤርትራዊ ጋር! ከቅዱስ መሀሉ

ጨዋታ ከፈጣኑ ኤርትራዊ ጋር! ከቅዱስ መሀሉ
ዛሬ አንድ ልጅ እኔና ሌሎች ሁለት ሰዎች ወደተቀመጥንበት ቦታ መጥቶ አጠገቤ ቁጭ አለ። ልጁ በጣም ፈጣን ነው። “ምን ፈልገህ ነው? ታውቀኛለህ?” ብየ አይን አይኑን እያየሁ ጠየኩት። “አንገቱን ሰበር አድርጎ በናትህ እርዳኝ። ኤርትራዊ ነኝ። 7ዓመት ትግራይ ውስጥ ሽመልባ የስደተኞች ካምፕ ኖሪአለሁ። አስፈቅጄ ለጉዳይ መጥቼ ነው። አሁን ወደዚያው ልመለስ መሳፈሪያ አጥቼ ነው። ቦሌ አካባቢ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ስደተኞች ካምፕ ሊረዳኝ አልፈቀደም እንጅ ማመልከቻ አቅርቤ ነበር።ካላመንከኝ ይሄው መታወቂያየን ተመልከት” ብሎ እጁን ዘረጋ። “የእኔ ማመን እና አለማመን ለምን አስፈለገህ። ያንተ መታወቂያ ማቅረብ እኔ ገንዘብ እንድሰጥህም ሆነ እንድከለክልህ አያደርገኝም። በአጭሩ ገንዘብ አልሰጥህም።ስለዚህ ወደ ሌላ ቦታ ሂደህ ጠይቅ።” አልኩት። “አልሄድም። አንተ ትሰጠኛለህ።በናትህ አንተን ለመጠየቅ ስላልከበደኝ እንጅ አካባቢው ሁሉ እንደምታየው ሰው ነው። ግን አለምንም!” አለኝ። “እንዴ! እኔ ኪስ ገንዘብ ባይኖርስ? ብይዝም ደግሞ ለሌላ ጉዳይ እንጅ መቼም ላንተ ለመስጠት አቅጄ እንደማልይዝ ይገባህል።ስለዚህ•••” “አረ በእግዚአብሄር ስጠኝ። ስታየኝ ሱሰኛ ብመስልም ላታልልህ ግን አይደለም። ቸግሮኝ ነው። ለመኪና መሳፈሪያ ብቻ ነው የምፈልገው?” ሲል ተማጸነኝ። ጊዜ ቢኖረኝ ኖሮ የመኪናውን ትኬት እራሴ ልቁረጥልህ ልለው አስቤ ነበር። ግን ያን ማድረግ ስለማልችል የልጁን እውነተኛነት ለማጣራት ትንሽ አወራን። ልጁ ሲያወራ ልክ እንደሚግባቡ ጓደኛሞች እንጅ ድንገት ያውም ገንዘብ እርዳኝ ሊለኝ የተጠጋ ሰው አይመስልም። ግማሹን ገንዘብ ከኔ ወስዶ የተቀረውን አብረውኝ ካሉ ሰዎች እንዲጠይቅ ብጠይቀውም “አይ!ከሌላ ሰው አልፈልግም። ከሰጠህ አንተ ስጠኝ?” አለኝ። ይሄ መታወቂያ የውሽት ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ ደህንነት ትሆናለህ” ስለውም “አንተ ደህንነት የሚፈልግህ ሰው ነህ እንዴ? አሁን እኮ ብሩን እንደሰጠህኝ እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ ደህንነት ቢሮ እሄዳለሁ። የይለፍ ፍቃድ የሚሰጡኝ እነሱ ናቸው። አንች ጋር ካዩኝ አሜሪካየን ውሃ በላት ማለት ነው።” አለኝ። “አሜሪካ ደግሞ እዚህ ምን አመጣት?” ስል ጥያቄየን አስከተልኩ። “ሰባት አመት በስደተኛ ካምፕ ውስጥ የምንገበገበው እሷን ተስፋ አድርጌ ነው።አለዚያ ለምን እኖራለሁ?” እንደገና ጠየቀኝ። ይሄን ጊዜ መታወቂያውን ልብ ብየ ማየት ጀመርኩ። ስሙን እስከናያቱ፣የትውልድ ቀንና ቦታ፣መታወቂያ የተሰጠበት ቀን እና ፎቶውን በደንብ ተመለከትኩት። በርግጥም እውነተኛ ነው። “አንተ ግን ምናልባት በኤርትራዊያን እግር እየተተኩ ከሚሄዱትና የባለስልጣናት ዘመዶች ከሆኑት የትግራይ ልጆች አንዱ ብትሆንስ በምን አውቃለሁ። እነሱም እኮ አንዴ የዩኤንኤችሲአር መታወቂያ እስኪያገኙ እንጅ እንዳንተ አዲስ አበባ ነው የሚኖሩት።” አልኩት። “አንተ ብዙ ታውቃለህ።ብዙ ብዙ•••።እኔ ግን አንተንም ስለማላውቅህ ስለዚህ ጉዳይ አላወራም። እኔ አንተ የምትላቸውን ዓይነት ሰዎች ብሆን ካንተ ገንዘብ የምለምን ይመስልሃል? አዲስ አበባ ከመጣሁ ሶስት ሳምንቴ ነው። የመጣሁት እዚያ ሰልችቶኝ ትንሽ ስራ ልስራ ብየ ነበር።እሱም አልተሳካም። ስለዚህ በአስቸኳይ መመለስ ይኖርብኛል። ለመመለሻ የሚሆን ገንዘብ እርዱኝ ብላቸውም ዝም አሉኝ።” በማለት ቀለል አድርጎ መለሰልኝ።

“ገንዘቡን ብሰጥህና ዛሬ ለሌላ ነገር ብታጠፋውስ?” የኔ ጥያቄ ነበር። “አላጠፋም። ለምን አጠፋለሁ? የሲጋራ ሱስ ብቻ ነው ያለብኝ። እሱን ደግሞ ገንዘብ ሰጠህኝ አልሰጠህኝ የሚቀር አይደለም።” የሱ ምላሽ ነው። “ማለቴ ገንዘቡን አጥፍተህው ነገ እዚህ በድጋሚ ስትለምን ባይህስ?” ብየ ስጋቴን ገለጽኩለት። “ ያው ሰላም እልሃለኋ! ሌላ ምን ይባላል።” አለኝ። ሳቄም መጣ፤ተናደድኩም። “እንካ መታወቂያህን፤አልሰጥህም በቃ!” አልኩት። ልጁ የሚላቀቅ አይነት አይደለም። “በዚያ ላይ ለሻቢያ ተላላኪ ገንዘብ ረዳህ ብባልስ? የሻቢያ ተላላኪ አለመሆንህን በምን አውቃለሁ? ስለዚህ አልረዳህም።” አልኩት። “ግዴለህም ትረዳኛለህ። በመሃል አዲስ አበባ እንደዚህ መንቀሳቀስ የሚችል የሻቢያ ተላላኪ ካገኘህማ ልትረዳው ይገባል። በልጦ ተገኝቷል ማለት ነው።ስለዚህ እሱንም ዓይነት ካገኘህ እርዳው።” በማለት እርዳታ ሊጠይቀኝ የመጣው ሰው ሙግት ገጠመኝ። ልጁ ያለው በራስ መተማመን በጣም ደስ ይላል። እኔም ለጨዋታ ተመችቶኛል። “ኢትዮጵያዊ እንደነበርክ ግን ታውቃለህ? ወደፊት ኢትዮጵያዊ ብትሆንስ ደስ ይልሃል?” ስል ጥያቄ አከልኩለት። “እኔም አንተም ያንድ ሃገር ዜጎች ነበርን። አሁን ግን አይደለንም። ኤርትራ ሆኜ ሳስበው ኢትዮጵያዊ ሆነን በቀረን ኖሮ እል ነበር።ኢትዮጵያ ይች የማውቃት ከሆነች ግን (ወደ ጆሮየ ጠጋ ብሎ) ትቅርብኝ።” አለኝ።

ልጁ የሚያወራው በቀጥታ እና በፍጥነት ነው። “በል እንካ ሃምሳ ብር•••ሌላውን ከሌላ ሰው ጠይቅ?” ብየ አጠገቤ ያሉትን እና የግል ጨዋታቸውን ከሚያደሩት ጓደኞቼ “ይሄ ልጅ ኤርትራዊ ነው።የመኪና መሳፈሪያ ገንዘብ እየጠየቀኝ ነው።እኔ 50ብር ልሰጠው ነው።እናንተም ጨማምሩና ይሂድ።” አልኳቸው። “50ብር ከሰጠህው መቼ አነሰው።አጭበርባሪ ይሆናል•••።እምቢ ካለ ይተወው•••” ሲሉ አናደዱኝ። አንድ ብር እንኳ ከኪሱ ያወጣ አልነበረም። ትንሽ ገንዘብ ይጨምሩለታል ብየ የሰው ዓይን እፈራለሁ ያለውን ልጅ ይበልጥ ያሸማቀቅኩት መስሎ ተሰማኝ። የገንዘብ እርዳታ እየጠየቀኝ እንኳ ከኔ ሃሳብ እና ጥያቄ ጋር ለይምሰል እየተቅለሰለሰ እንዳብዛኟው ሰው ሊያስመስል ያልፈቀደው ወጣት ልበሙሉነት አስደስቶኛል። የማያምንበትን ሃሳብ ሊቀበል ቀርቶ ጭራሽ ሙግት እየገጠመኝ ነው። ምናልባት መልስ ሰጠኝ ብሎ ገንዘብ ይከለክለኝ ይሆን እንዴ?ብሎ ያሰበውን እና የመሰለውን ከመናገር አልተለጎመም። ይህ አስመሳይነትን እና ማጎብደድን ያልለመደ የሰው ባህሪ ነው። ደስ አለኝ። ስለዚህ የራሴን ሰዎች ተውኩና ወደ ልጁ ዞሬ አንድ ነገር እንስማማ አልኩት። “እሽ!ምንድ ነው?”አለኝ። “መታወቂያህን በሁለቱም በኩል ፎቶ ላንሳው። ከዚያ ገንዘቡን እኔ ልስጥህ። ነገ በዚህ አካባቢም ይሁን በሌላ ቦታ ካየሁህ ግን መታወቂያህን ከፎቶህ ከነስምህ የመታወቂያ ቁጥር እና የትውልድ ቀን የሚገልጸውን ክፍል በማህበራዊ ድረገጽ አሰራጭቼ አጭበርባሪ መሆንህን እንድናገር ፍቀድልኝ።” አልኩት። ማለትም ድንገት እያጭበረበረ ከሆነ በፎቶው የምታዩትን መታወቂያ የፊትለፊት ገጽ እንድለጥፍ ይስማማ እንደሆን ጠየኩት። ጥቂት በትካዜ ካሰበ በኋላ “እሽ ችግር የለውም። አንተ መቼም ለተንኮል ያን የምታደርግ አትመስልም። ያን የሚያደርጉ ክፉ ሰዎች ያስታውቃሉ።መጀመሪያውኑ ፊታቸውን አይቼ አውቃቸዋለሁ።ገንዘብ ወስጄ የምታገኜኝ ከሆነ ያልከውን ሁሉ ብታደርግ አልከፋም። ይገባኛል።” በማለት ቃል ገባልኝ። ስምምነታችንም በዚሁ ቃልኪዳን መሰረት ተግባራዊ ሆነ። ስሜን ጥየቀኝና “መቼም አልረሳህም!”ብሎ ተሰናበተኝ። እኔም ተሰናበትኩት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *