ግንቦት ሰባት ከገባበት የትግል ቅርቃር ውስጥ ለመውጣት ቢያደርግ የሚያዋጣው ( ሄኖክ የሺጥላ )

ግንቦት ሰባት ከገባበት የትግል ቅርቃር ውስጥ ለመውጣት ቢያደርግ የሚያዋጣው ( ሄኖክ የሺጥላ )

ከትችት ባለፈ እንደ ግለሰብ የሚታዩኝ ነገሮች አሉ ። ከውግዘት ባለፈ ቢደረግ ይጠቅማል የምለው አለኝ። ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ፥ የሁሉም ኢትዮጵያኖች ሃሳብ ተጨምቆ ለክርክር እና ለሙግት ቢቀርብ ፥ አሁን እየተጓዝንበት ካለው የተሻለ መንገድ ይኖራል ባይ ነኝ ። እዚህ ሃገር brain Storm ይሉታል ። እሱን ማድረግ ያስፈልጋል ። በድጋሚ ።
ትሞክራለህ ፥ የሞከርከው እንዳቀድከው ኣልተጓዘም ሌላ መንገድ ትፈልጋለህ ። አይ ትናንት ይሄንን ብዬ ደሞ ዛሬ እንዴት ይህንን እላለሁ የምትል ከሆነ ግን አንተም እንደቀደሙት ትወድቃለህ ። ውድቀትህን ስለማልመኝ የሚሰማኝን እንደሚከተለው አቀረብኩ ። ልክ ነኝ ማለቴ ግን አይደለም ፥ በጥቂቱ የሚሰማኝ ይሄ ነው ማለቴ ግን ነው።

ግንቦት ሰባት ከገባበት የትግል ቅርቃር ውስጥ ለመውጣት ቢያደርግ የሚያዋጣው

1ኛ ) ኤርትራን እንደ ብቸኛ መጠጊያ አድርጎ ማየቱን ማቆም ! ማቆም ብቻ ሳይሆን ክፍት ሜዳዎችን ማሰስ ። ክፍት ሜዳዎች የምላቸው በአደጋ የተሞሉ ግን ለለውጥ የሚተቅሙትን ነው ። ለምሳሌ ኦጋዴን ውስጥ ትግል እና ታጋዮች አሉ ፥ በሱዳን በኩልም ይህ እየሆነ እንደሆነ እንረዳለን ፥ ኬኒያም ብትሆን ትክክለኛው የፖለቲካ ስራ ከተሰራ የማታግዝበት ምክንያት አይታየኝም ። ከዚያ በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያለውን የ ወታደራዊ ካምፕ ማደራጀት ፥ መጨመር እና ማብዛት የወያኔን ሃይል ይበትነዋል ። በኢትዮጵያና ኤርትራ ድምበር ላይ ትግሉን እንዳይቀላቀሉ ሲል የሚጠባበቃቸውን ሰዎች መውጫ ቀዳዳ መጨመር ብቻ ሳይሆን ፥ ሃሳቡን ሰብስቦ በኣንድ መልካ ምድር ላይ አይኑን ( ሃይሉን ) እንዳይጥል ያደርገዋል ። ለምሳሌ ከግብጥ እስከ ሱዳን ሊዘረጋ የሚችል ወታደራዊ ሰንሰለት ለማበጀት ማሰብ አንዱ ይመስለኛል ።

2ኛ) ለወያኔ ወይም ከወያኔ ጋ ሊወግኑ የማይችሉ ወዳጆችን በመምረጥ ፥ ወታደራዊ ስልጠና እንዲሰጡን መጠየቅ ። ኔልሰን ማንዴላ አዲስ አበባ መጥቶ ነው ስልጠና የወሰደው ። ዝንቧቤን እንደ አንድ የጦር ካምፕ መውሰድ የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ። በዚህ አኳያ ሊረዱ የሚችሉ ብዙ አቅም ያላቸው ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን ።

3ኛ) የህውሓት ማዕከላዊ የስልጣን መሰረት የሆኑትን ሰዎች የለት ተለት ኑሮ ፥ ጥበቃ እና ኣቅም የሚያጠና ቡድን መመስረት ። ስራው ስለነዚህ ሰዎች እንቅስቃሴ ክትትል የሚያደርግ ብቻ ነው ። እንዴት ያደርገዋል ፥ እሱን መነጋገር እንችላለን ።

4ኛ) በውጭ ሃገር የሚደረገውን ለውጥ ያላመጣ ተቃውሞ ፥ ለውጥ ሊያመጣ ወደሚችል እንቅስቃሴ መምራት ። ይሄም እንዴት ሊሆን ይችላል ለሚለው ግራ ስለገባችሁ ጠይቁን ፥ ከናንተ ባንሻልም እናንተ የማታይቱን እንደምናይ ግን ገምቱ!

ሁል ጊዜም መታሰብ ያለበት አብይ ጉዳይ ግን ፥ ሻዕቢያን በሽራፊ ፍቃደኛነቱ ላይ መጫን የሚቻለው ኤርትራን መሰረት ያላደረገ እንቅስቃሴ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል በማሳየት ብቻ ነው ! ሻዕቢያ ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ተናግረን ፥ አምነን እና ተቀብለን የምናደርገው ትግል ሁል ጊዜም በሻዕቢያ በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነው የሚሆነው። ይሄ ደሞ የላጋሽ እና የተለጋሽ መንፈስን ስለሚፈጥር ብቻ ሳይሆን ሲፈቀድ ጠብቆ መታገል በምንም አይነት ለድልም ስለማያበቃም ጭምር። ማሸነፍ የሚፈልግ አማራጩን ያብዛ ። አማራጭ ከሌለ አማራጭ ይፍጠር ። መንገድ የለም ያለው መንገድ አንድ ነው ብሎ የሚዋጋ ጀነራል ውጊያውን ሳይጀምር ነው የተሸነፈው ! ይታሰብበት ፥ ይመከርበት ፥ የሚችል ( አቅሙ ያለው ይሳተፍበት )። ጦርነት ጥበብ ነው ፥ በጥበቡ ላይ የተካኑ ሰዎች ወደፊት ይመጡ ዘንድ ይጋበዙ ፥ ሻዕቢያን ላለማስቀየም ሲባል የተገፉት ሰዎች በሚስጥር እናዋያቸው ። ያውቃሉ ፥ ይችላሉ ፥ ለውጥም ያመጣሉ ።

እጃቸውን አጣምረው 10 አመት ተራራ የሚያዩ ታጋዮቻችን አንበሶች እንደሆኑ ጠላቶቻችን ያውቁ ዘንድ መንገዳችን ድጋሚ ይመርመር !

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *