ስም መቶ ብር ፥ ስራ ኣንድ ብር !

ስም መቶ ብር ፥ ስራ ኣንድ ብር ( ሄኖክ የሺጥላ )

የመሰንቆው ሊቅ ፥ የጥበቡ ገበሬ ጋሽ ጌታ መሳይ አበበ

«የሽምብራው ጠርጥር የዛፎቹ ፍሬ
የትም የትም ዞሬ ትዝ ኣለኝ ሃገሬ » የምትል ሃረግ ( ስንኞች) ያዘለች ዘፈን አለችው ። ልጅ እያለሁ ታያቴ ጋር እሁድ ተ ቤተስኪያን መልስ በብረት ምጣድ ላይ የተንገረገበ አሹቅ እየበላን ዘፈኑን ስናዳምጥ ይሰማኝ የነበረውን ስሜት ዛሬም ድረስ ኣልረሳውም ። አንዳንዴ እንደውም በከፍተኛ ምስጠት ውስጥ ወድቄ « ጋሽ ጌታ መሳይ በልጅነቱ እንደኔ የ ባኤላ ( ባቄላ ) አሹቅ ነው በልቶ ያደገው ማለት ነው እላለሁ ። በወቅቱ ዘፈኑን ሳዳምጥ ይሰማኝ የነበረው ነገር ፥ ያንን በብረት ምጣት ኣጉል ታምሶ የሜዳ ኣህያ የመሰለ ባቄላ ከኛ ቤት የሚያጠፋልኝን ነገር ምን ይሆን እያልሁ ጠሎት በያዝኩበት ወቅት ፥ ጌታ መሳይ « የሽንብራው ጠርጥር የዛፎቹ ፍሬ » እያለ ሽንብራ እንደናፈቀው ሲናገር ፥ « ሰው ካልጠፋ ነገር ስለ ኣሹቅ እንደ ትልቅ ትዝታ ቁም ይዘፍናል እያልኩ ተራሴ ጋ ኣወራ ነበር ። እያቴም ልክ አይስክሬም ሲበላ ከርሞ ከብዙ አመት በኋላ ባቄላ የበላ እስቲመስል ድረስ ዘፈኑን « እህህ!» እያለ ነበር የሚያዳምጠው ። በጌታ መሳይ ዘፈን እና ሴት ኣያቴ ከፊት ለፊቱ ቀድታ ባስቀመጠችለት በ ክብር ዘበኛ ኩባያ ኣፉ ድረስ የተሞላውን ቀሪቦ መሃከል የተሰጣውን የባቄላ ኣሹቅ እየቃመ እንደ በርሃ ግመል ከተቀዳለት ከንፈሩን ገጥሞ እየመጠጠ ፥ በጌታ ምሳይ ላይ ደሞ ማሞ ኣየልን ጣልቃ እያስገባ « በል ተነስ እንተኛ የኔ ሃሳብ ጓደኛ አለ ማሞ አየለ »
እሁዴን በድን ያደርግብኛል ። ይሄ የኣያቴ ለባቄላ መመሰጥ እና የጌታ መሳይ ለሽንብራ መዝፈን በጣም ያበሳጨኝ ስለነበረ « በኣሹቅ ኪንግደም ወስጥ እየኖሩ ስለ ኣሹቅ በትዝታ መመሰጥ ኣሁን ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው» እያልኩ ደግሜ ደጋግሜ በልቤ እጠይቅ ነበር ። ይህ የአያቴ ባቄላ እየበሉ ባቄላ ትዝ ኣለኝ ብሎ የመመሰጥ ታሪክ የህዝባችን ታሪክ እንደሆነ የገባኝ ግን እጅግ በጣም ፥ በጣም ቆይቶ ነው ።

ለምሳሌ
እንዲህ እንደኔ መዞር እና መንከራተት እጣ ፈንታው ለሆነ ትውልድ ፥ ሃገሩን ለማስታወስ የሽንብራ ጠርጥር ወይም የሰነፍ ገብስ ቆሎ ማወደስ ይጠብቀበታል ?
«ታፍራና ተከብራ የኖረችው ሃገራችን» የሚለውን ሆኖ ሳይሆን ሰምቶ ያደገ ወሴፋ እና ወሬዛ ፥ ውርደት የመቀበል ኣቅሙን ያገኘው ከዚሁ « ከሽንብራ ጠርጥር ፥ ከዛፎቹ ፍሬ » ኣይደለምን ? እንደውም ኣብዛኛው የሃበሻ ማንነት በጆሮ የተንቆረቆረ ምንነት ነው የሚመሰለኝ ። ባልሰራነው ታሪክ ብቻ ሳይሆን በተቀማነውም ታሪክ እንሸልላለን ። ለዚህም ኣንዱ ማሳያ በምርጫ 1997 በመስቀል ኣደባባይ ወጥቶ የነበረውን የቅንጅት ደጋፊ ዛሬ በ 2008 የ ፌስ ቡክ የፕሮፋይል ምስል ኣድርገን እንለጥፋለን ። ሰው እንዴት በተሸነፈበት ታሪክ ይኮራል ? ከተግባር ይልቅ ወሬ እንወዳለን ። ለምሳሌ በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ፉከራ እና ሽለላ ለድርጊት የመዘጋጃ ወይም ደሞ የድርጊት መከወኛ ፥ የሞራል ማንቂያ ፥ የልብ ቃል መጠበቂያ እና የማህበረሰቡ የወኔ ቃሎች ነበሩ ። ጠላቶቻቸውን ለመግጠም ጦራቸውን ሲነቀንቁ ፥ ጋሻቸውን ሲሰብቁ ፥ የወንድ ደማቸው በፈጠረው እልህ፥ ኣልደፈርም እና ኣልበገርም ባይነት ይሸልላሉ ። እምቢ ሲሉ ፥ ኣረቄ ቤት ቁጭ ብለው የኮማሪ ጭን እየመቱ ፥ ወይም ባህር ማዶ የነጩ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት እየጮኹ ሳይሆን ፥ ባገራቸው ኣፈር ላይ ፥ አቀበት በጥፍሮቻቸው ቆንጥጠው ፥ ከጠላት ፊት ቀጥ ብለው ቆመው ፥ ከድርጊታቸው በፊት እና በኋላ የሚያደርጉት ነገር ነበር ። ለዚህም ይመስለኛል « ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም » የሚለው ዘፈን « ባትዋጋ እንኳ በል እርገፍ እርገፍ ፥ ያባትህ ጋሻ ትሗኑ ይርገፍ » ከሚለው በተሻለ የሚቀነቀነው። ምክንያቱም « የሚካኤል ስለት ለገብርኤል ምኑ ነው » እንደሚሉት ማለት ነው ። ኣባቶቹን በማስታወስ ራሱን የረሳ ትውልድ ከዚህ ሌላ ምንም ሊሰራ ኣይችልም ! በኣባቶች ታሪክ የሚኮራ ፥ የራሱን ታሪክ የማያውቅ ትውልድ ያለ ምንም ጥርጥር ለምን በኣባቶቹ ታሪክ እንደሚኮራ ቢጠየቅ ይህ ነው የሚለው ምክንያት ስለመኖሩ እጠራጠራልሁ ። አድዋን የሚያከብር ፥ ጎንደር ተቆርሶ ለሱዳን ሲሰጥ ኣንዳች የማይሞቀው ህዝብ ኣድዋን ያከበረበትን ምክንያት ያውቀዋል ለማለት እቸገራለሁ ። የ ኣምስት ኣመት የኣበኞች ተጋድሎን በኩራት የሚያወራ ትውልድ ፥ እሱ ግን ለያንዳንዱ ችግር እንደ መፍትሄ የወሰደው ሃገር ጥሎ መሰደድ ከሆነ ፥ ስለ ኣርበኞችም ያወራው ኣፉ ላይ መጥቶለት እንጂ በእውነት ገብቶት ነው ለማለት ይከብዳል ። « ኢትዮጵያ ሙሉ በሙል ነገ ልትቃጠል ነው » ተብሎ ቢታወጅ ፥እሳቱን ለማጥፋት ከመቆም ይልቅ ፥ ኣጎዛውን ይዞ ኬኒያ እና ሱዳን ጠረፍ ላይ ተቃጥላ እስክትጨርስ መተኛትን የማይመርጥ ትውልድ ስለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለን ? ተማርን የሚሉት ፥ ትምህርትን የሚቀበሉበት መንገድ የሞራል ልዕልናን የነጠፈ ስለሆነ ፥ እውቀቱ ከሚያመጣው ዘኬ ለመቃረም በየ ሃገሩ በር ላይ ለቪዛ ሲጋፉ ይታዩ ይሆናል እንጂ ፥ ይሄ « ሳይማር ያስተማረን ትውልድ » እያሉ የሚያላግጡበት ገበሬን ከሳር ክዳን ለማውጣት ኣንዳች ሃሞቱ ያላቸው ኣይደሉም ። ይልቁንም ጡረታ ሲወጡ በወጣትነታቸው ደሙን የመጠጡትን ህዝብ ፥ ሲያረጁ ደሙ በጥናታዊ ፅሁፍ ስጋው ቆርጠው ይበሉታል ፥ መሲህ እና ባለ በትረ ኣሮን በመምሰል ፥ የሟሟ ኣጥንቱን በ ጉም ተስፋቸው ይጠቡታል ።

በስደት ላይ ሃገሬ ሃገሬ እያለ የሚያለቅሰውም ሆነ ፥ ሃገሩ ቁጭ ብሎ ስደት ስደት እያለ በየ አድባራቱ እና ገዳማቱ ባለ ወርቀ ዘቦ ዣንጥላ እና የአበባ ምንጣፍ ስለት የሚያስገባው ሁሉም ሲሳካለት ፥ ለሃገሩ ረብ ያለው ነገር ከማድረግ ፥ የህዝቦቹን ህይወት ከመለወጥ እና ታሪኬ እያለ ጉሮሮውን ከሚሰነጥቅለት ታሪክ የሲሶ ሲሶውን ከመተግበር ይልቅ « የሽንብራው ጠርጥር የዛፎቹ ፍሬ » እያለ ፥ የልጅነት ድህነቱን ያገር ፍቅር መመሰጫ ያደርግብሃል ! በሰባራ ምጣድ የተጠፈጠፈ ለሴ ፥ በጭራሮ የተጋገረ እንጀራ የችጋር ውጤት ሳይሆን የባህል ውጤት እንደሆኑ ኣድርጎ ፥ አመዱ ፥ የወንዝ ውሃው ፥ በኣህያ ተጭኖ ይመጣ የነበረው ኣሞሌ ጨው እያለ ሸሽቶት የሄደውን ድህነት ባህሉ እና ማንነቱ አድርጎ ያወራልሃል ። በእንስራ ውሃ መቅዳት ፥ ወደ ጀሪካን እና ባሊ መሻገር የሚችል አእምሮ እጥረት መሆኑ ተረስቶ ፥ እንደ ኣንድ ቅርስ በየ ገባህበት ተለጥፎ ታየዋለህ ፥ ከሁለት በሬዎቹ ጋ የሚታገል ገበሬ ፥ በፍቅር ሳይሆን በጅራፍ የሚሰሩ ሰንጋዎቹን ከፊት ኣስቀድሞ ሲያርስ የሚያሳይ ፎቶ ከግድግዳ ኣልፎ የብር ኖቶች ላይ ተስሎ ታያለህ ፥ ባንፃሩ የማንነትህ መገለጫ የሆኑ የሃገር ድንበሮች ፥ የባህር በሮች እና ወዘተ በየትኛውም የመገለጫ መድረኮች ውስጥ ቦታ ሲሰጣቸው ኣታይም ። እስኪ ኣስቡት ዳቦ በወረፋ ፥ ዘይት በ ቤራንቲን ብልቃት ገዝቶ ያደገ ልጅ
« ኣሳድገሽኛል ኢትዮጵያ
በማር በወተት እማማ
ኢትዮጵያዬ እማማ
ምድራዊ ገነት »
የሚለውን ዜማ ሲሰማ ምን እንደሚሰማው ኣስቡት ! ለነገሩ በእንደዚህ ኣይነት ህይወት ውስጥ እንደዚህ ኣይነት ዘፈን ሰምተን ስላደግን ይመስለኛል ፥ ዛሬም ሺዎች እንደ ቅጠል እየረገፉ « እሱ ያመጣውን እሱ ይመልሰው » እያልን የምንኖረው ። እሱ ማን ነው ግን ? እኛስ ማን ነን ? ስራችን እና ስማችን ፍጡም የማይገናኝ ። ሽለላችን እና ልባችን ፍጡም የተራራቁ ፥ ህይወታችን በኑሯችን የማይገለጥ ፥ ምን ኣይነት ምስጢሮች ነን ግን ?
ስም መቶ ብር ፥ ስራ ኣንድ ብር ነው ያሉት የኣዱ ገነት ልጆች !

ቸር እንሰንብት ( ሄኖክ የሺጥላ )

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *