አማራ ነኝ ስል ፥ ኣንዳንዶች ደነገጡ ፥ ኣንዳንዶች ተቆጡ ። አማራ ነኝ ስል ፥ ኣረ ተው ተመለስ ኢትዮጵያ ነህ ብለው ለመስበክ ሞከሩ

አማራ ነኝ ስል ( ሄኖክ የሺጥላ )

አማራ ነኝ ስል ፥ ኣንዳንዶች ደነገጡ ፥ ኣንዳንዶች ተቆጡ ። አማራ ነኝ ስል ፥ ኣረ ተው ተመለስ ኢትዮጵያ ነህ ብለው ለመስበክ ሞከሩ ። ኣይንህ የሃገር ነው ያንተ ፥ እንደ ኢትዮጵያ ስታስብ ነው የሚያምርብህ ኣሉ ፥ ገዘቱ ኣስገዘቱ ። ምክራቸውን ሰማሁ ፥ ለቅሷቸውን ኣደመጥኩ ። አንዳዶች እዚህ ሃገር ( ዌዲንግ ብሮከር ) ወይም ድንኳን ሰባሪ እንደሚባለው ኣይነት ፥ በኣንድ የድርቅ ማሰባሰቢያ ላይ ግጥም እንዳቀርብ ተጋብዤ ከኔ ቀድመው የመናገር ( «የመለፍለፍ ») እድል ኣግኝተው ስለነበር ፥ ኣንድነታችንን ለማፍረስ ኣትስሩ ፥ ወያኔ በቀደደው ቦይ ኣትፈሱ ብለው በኣግድሞሽ እና በገደምዳሜ ( tangentially ) ሊቆጡ እና ሊያስፈሩ ሞከሩ ። አማራ ነኝ ማለት እንዲህ እንደሚያስፈራ ኣላውቅም ነበር ። ይደንቃል ።

ልደግምላችሁ መሰለኝ? ኣዎ አማራ ነኝ ። አማራ ብቻ ሳልሆን በአማራነታቸው ፍፁም ከማያፍሩት ውስጥ ነኝ! ከማያፍሩት ውስጥ ብቻ ሳይሆን አማራን አንድ ኣድርጎ ለድል ከሚያበቁት ውስጥም እንደሆንኩ ብነግራችሁስ ? እናንተ የኔ « ነኝ» ነው ያስጨነቃችሁ ? ገና ነን የሚሉ ሚሊዮኖች እንዲፈጠሩ እሰብካለሁ ፥ደሞም ይሳካልኛል ። ለምን ቢሉ በልባችን ክፋት ስለሌለ ። ማንንም የበታች እና አናሳ ነው ብለን ስለማናስብ ፥ ማንንም ለማጥፋት ሳይሆን አማራን ለማዳን መስራት እንዳለብን መግባባት ላይ ስለደረስን ። ወያኔ የቀደደልን ቦይ አማራ ነኝ የሚለውን ኣይደለም ፥ ወያኔ የቀደደልን ቦይ ፥ አማራ ነኝ ብዬ ሌሎችን ከማስቀይም ኣማራ ይሙት የሚለውን ነው ። እኔ ደሞ እሱን ለመድፈን ነው የተነሳሁት ። ድሉን ኣብረን እናየዋለን ። በእርግጥም የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን በቁማቸው ፥ ሳይሞቱ እናሳያቸዋለን ።

ከነዓን ለመድረስ የፈጀው ኣርባ ኣመት
ኣርባ ቀን ነበረ ፥ እምነት እና ፍቅር ፥ እውነት ቢኖርበት !

ድል ለአማራ ህዝብ !

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *