ስብሃት ለኣበበ ገላው ፥ ወ ስብሃት ለ ሴራው! ( ሄኖክ የሺጥላ )

ስብሃት ለኣበበ ገላው ፥ ወ ስብሃት ለ ሴራው! ( ሄኖክ የሺጥላ )

ኣበበ ገላው የኢሳት ፊት ኣውራሪ ሆኖ በቀጣይ እንዲያገለግል መቀባቱን ሰምተናል ። ሹመቱ የሳኦል ኣይነት ሳይሆን የዳዊት ኣይነት ሊሆን እንደሚችል ገምተናል ።

ኢሳት መንግስታችንን በከባድ ሚዛን ለመገዳደር እንዳሰበ የሚያሳብቅ ሹመት እንደሆነ ከኣበበ ጋ የተፋለሙት የባዶ ዲግሪ ሊሂቃኖች ይመሰክራሉ ። አበበ ገላው ለኛ ለኢትዮጵያዊያኖች ትልቅ ባለ ውለታችን ስለመሆኑ ደግሞ ደጋግሞ ተጥፏል ። በምድር ላይ ሰይጣንን ያስደነገጠ ብችኛ ሰው ለኔ አበበ ገላው ይመስለኛል ። እርግጥ አበበ ገላው ያደረገልን ( የዋለልን ውለታ ) ሁሉም ጥሩ እና በጎ ነበር ማለት ላይቻል ይችላል ። ለምሳሌ ድሮ ልጆች እያለን በነፃነት አበበን ለ ዓርፍተ ነገር መስሪያ እንጠቀምበት ነበር ፥ ኣሁን ግን ኣበበ ፥ ኣበበ የሚለውን ስም ዋጋ በማናር « አበበ በሶ በላ » ከሚለው « ኣበበ እነ መለስን በላ » « ኣበበ ገና እነ ስብሃትን ይበላል » ወደተባሉ ረቂቅ እና ለተራው ሰው የማይገቡ ኣርፍተ ነገሮች መጠቀሚያ ሆኗል ። ይህም ኣበበ የሚለው ስም ከበሶ ማባያነት ወጥቶ ፥ በምትኩ ልጆቻችን « ሃይለማሪያም ቦርዴ ጠጣ » የሚል ኣዲስ ኣርፍተ ነገር ስርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ተካቶ እዲማሩ ተደርጓል ። ኣበበ በሶ በመብላት ያጠፋ የነበረውን ጊዜ ወደ ጎን ገፋ ኣድርጎ በምትኩ ዱቄት የሆኑ መሪዎቻችንን እየፈጨ ለቀብር ሬዲ እንደሚያደርግልን ባለ ሙሉ ተስፋ ነን ።

ኣበበ ገላው ብዙ ጥሩ የሆኑ ባህሪዎች ኣሉት ። ለምሳሌ ማሴር ( conspire ) ማድረግ እንደሚችል በደንብ ኣውቃለሁ ። ይህም ማለት ምን ማለት ነው ኣንተ መቼ እና እንዴት እንቅልፍ እንደሚወስድህ በደንብ ያውቃል ማለት ነው ። ከኣበበ ኣጠገብ መተኛት ምን ያህል ኣደገኛ እንደሆነ የተረዳሁት ፥ እዚህ ካሊፎርኒያ ኣብረን በነበርንበት ጊዜ ኣንዳንዴ እየተገናኘን ስንጫወት « ሌሊት ላይ ይሄ ሃሳብ መጣልኝ » እያለ ይለኝ የነበረውን ብዙ ገጠመኞችስሰማ ነው ።
ኣበበ ኢትዮጵያዊ ሆነ እንጂ ራሺያዊ ቢሆን ኖሮ ቭላድሚር ፑቲን መገልበጥ የሚችለው እሱ ብቻ ይሆን ነበር ። ምን ለማለት ነው ባጭሩ ኣካባቢው ያለውን ነገር በጥንቃቄ የሚያጤን እና የሚመረምር ሰው እንደሆነ ደርሼበታለሁ ። እንዲህ ኣይነት ሰው ማናጀር ኣድርገህ ስትሾም እንግዲህ ወየው « ለሲሳይ ኣጌና » ፥ « ወየው ለመሳይ » ፥ « ወየው ለካሳሁን ይልማ » ፥ « ወየው ለብሩክ ይባስ » ፥ « በጣም ወየው ለብሩክ ታይት እና ገሊላ » ፥ እነ ኣፈወርቅን እና መታሰቢያ ቀፀላን የምታውቋቸው ሰዎች ካላችሁ ቶሎ ኣዲስ ስራ ፈልጉ በሏቸው።

ኣበበ ገላው ብዙ ሰዎችን ከኦን ላየን የዲግሪ እና የትምህርት ፕሮግራሞች ኣውጥቷል ። እነ ኤርሚያስ ለገሰ ሳይቀሩ በስብሰባዎች ላይ ስለ ኦን ላየን ማስተርሶቻቸው ሲያወሩ እየሳቁ ብቻ ሳይሆን እየተሳቀቁ እንዲሆን ኣድርጓል ፥ ብዙ ሽቅርቅር ዶክተሮች የ ሊንክ ደን የዱክትርና ዱካ እና ገድላቸውን ኣጥበው እንዲያሰጡ ኣድርጓል ፥ ኣበበ በባዶ ሜዳ ይታበዩ የነበሩ የእንስሳ ዶክተሮች ፥ ዶክተሮች ሳይሆኑ እንሰሶች መሆናቸውን ኣጋልጧል ፥የትምህርት ደረጃቸው ሰማይ ላይ የነበሩ ቁልምጥ ባዶዎች ባንድ ሌሊት ከትዬ ለሌ ወደ «ምንም» የትምህርት ደረጃ እንዲሸጋገሩ ኣግዟል ። ይህንን በማድረጉም ለኛ ምንም ዲግሪም ይሁን ድግር ለማናውቅ ሌጣዎች የእኩልነት ስሜት እንዲሰማን ኣድርጓል ። ስብሃት ለኣበበ ገላው ፥ ወ ስብሃት ለ ሴራው!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *